ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአ/አ ልደታ ከፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ አብነት ተብሎ የሚጠራው ሰፈር የተመረጡ ቦታዎች በኮሮና ቫይረስ የተነሳ አካባቢው በፀጥታ ኃይሎች ጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ መግባቱ ተነገረ።
በርካታ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተገኝተውበታል በተባለ አንድ መንደር ውስጥ ነዋሪዎች በቤታቸው ተወስነው እንዲቆዩ ከመደረጉ ባሻገር ማንኛውም ሰው ከቤት እንዳይወጣ፣ ከሌላ ስፍራ የሚመጡ ሰዎችም ወደ መንደሩ እንዳይገቡ ከፌደራልና አዲስ አበባ የተውጣጡ ፖሊስች ሲከለክሉ ተስተውሏል።
በልደታ ክፍለ ከተማ አብነት ሰፈር ያለውን ጥብቅ ቁጥጥር ተከትሎ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ አካባቢው የተጓዘው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ፖሊሶችን ይህ ነዋሪዎችን በቤት ውስጥ የማቆየት የኃይል እርምጃ ለምን ያህል ቀን እንደሚቆይ ቢጠይቅም፣ የፀጥታ ኃይል አባላቱ ትዕዛዙን ከመቀበል ውጪ መቼ ስፍራውን እንደሚለቁ እንዳልተነገራቸው አስታውቀዋል።
ዛሬ የአካባቢው ነዋሪዎች በመኖሪያ ቤታቸው ተወስነው እንዲቆዮ የተደረገበትን ሁኔታ አስቀድመው ያውቁ እንደሆን ደውለን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ምንም ዓይነት ቅድመ መረጃ እንዳልነበረ አስታውሰው ከትናንት ምሽት ጀምሮ ብዛት ያላቸው የፀጥታ ኃይሎች መታየታቸውንና ከሌሊቱ 10 ሰዐት ጀምሮ የፖሊስ አባላቱ ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን ገልፀዋል።
ስለ እግድ እርምጃው እስካሁን መንግሥት ይፋዊ የሆነ መግለጫ ባይሰጥም ዛሬ ከረፋድ ጀምሮ ከቤት እንዳይወጡ የተደረጉት የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ቀጥተኛና አስተማማኝ የላብራቶሪ ምርመራ ማድረግ መጀመሩን የገለፁት የአካባቢው ነዋሪዎች በምርመራው አበረታች ውጤት እስኪገኝ ድረስ ለ14 ቀናት በቤት ሊቆዮ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።