ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሰሞነኛው የትግራይ ሕዝብ አመጽ የተደናገጠው ህወሓት ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌለው አረና ትግራይ ፓርቲ አስታወቀ።
ህወሓት ከሕዝብ የተነሳውን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ህዝብን ለመከፋፈል ጥረት እያደረገ ይገኛል ያለው አረና፤ የዋጅራት አካባቢ ነዋሪዎች ነገ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ እና ስብሰባ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረጉ ናቸው በማለት አመጹ አድማሱን ማስፋቱን ጠቁሟል።
“ጥያቄ በሚያቀርቡ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ማስፈራራትና ዛቻ እየተፈጸመ ስለመሆኑ መረጃ አለን” ያሉት የአረና ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ጸጋይ፤ ዋጅራት በሚባል አካባቢ ሕዝቡ ድንበር በሚመስል ሁኔታ በአንድ ወንዝና ወረዳ ከወረዳ እንዲጣላ በማድረግ፣ ህወሓት ሕዝብን ለመከፋፈል እየጣረ ነው ብሏል።
የአካባቢው ነዋሪ እንዲህ ዓይነት የተንኮል ሥራን በጥንቃቄ ሊከታተል ይገባል ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ ሕዝቡ ችግሩን እያሰማ ያለበት መንገድ ነጻ ለመውጣት የሚያስችለው እንደሆነ አስታውሰው፤ ህወሓት የትጥቅ ትግል በጀመረበት ማይሀንሰን ደደቢት በተባለ አካባቢ ዛሬ ዘጠነኛ ቀኑን ያስቆጠረ ሰልፍ መካሄዱንም ይፋ አድርገዋል።
በህወሓት በኩል እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ ተቃውሞ እስካሁን መረጃው ታፍኖ እንዲቆይ ተደርጓል ያለው አረና ትግራይ ፓርቲ፤ በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ ህዝባዊ ሰልፎችም ቀደም ሲል መንገድ ተዘግቶ ታፎኖ እንዳይወጣ ሲደረግ እንደነበረም አስታውሰዋል።
ህወሓት በበኩሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ምንም ዓይነት የሕዝብ ተቃውሞ የለም ብሏል። ህወሓት ከዚህ በተጨማሪ እንዲህ ዓይነት የሀሰት ወሬ የሚነዙት ሰላማችንን የሚያውኩ ሚዲያዎች ናቸው ሲል ከኢቢሲ አንስቶ የበርካታ መገናኛ ብዙኃንን ስም በመጥቀስ በአሳሳችነት ፈርጇል።