በኮሮና ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ አለን ያሉ 40 ሰዎች ምርመራ በልመና ተሳካ

በኮሮና ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ አለን ያሉ 40 ሰዎች ምርመራ በልመና ተሳካ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና–  ትናንት የኮሮና ቫይረስ አለባቸው ተብለው ሪፖርት ከተደረጉ ሰዎች መካከል፣ ከአንደኛው ጋር ንክኪ አለን ያሉ 40 ያህል ሰዎች በራሳቸው ፍቃድ ሆስፒታል ሄደው  “መርምሩን” ቢሉም ሰሚ እንዳላገኙ ተሰማ።

ሰዎቹ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ የሄዱት ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሲሆን፤ አርባዎቹ ሰዎች ከሆስፒታሉ ደጃፍ ሆነው “ምርመራ አድርጉልን” እያሉ ከጠዋት ጀምሮ ቢማጸኑም ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘታቸውን ለሸገር ራዲዮ ገልጸዋል።
የሰዎቹ በመልካም ፍቃደኝነት ምርመራ ለማድረግና ከንክኪው ያለውን ውጤት ለማወቅ መጣራቸው የሚደነቅ ነው ያለው የቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ የኮሮና ቫይረስ ጋር ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን የመለየት ሓላፊነት ያለበት  ተቋም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መሆኑን በመግለጽ ከመ/ቤቱ ትዕዛዝ እስካላገኘ ድረስ ጥያቄውን መመለስ እንደማይችል አስታውቋል።
እነዚህ 40 ሰዎች ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ንክኪ አለን ወደ ሆስፒታል ያሉት በተለምዶ አውቶቢስ ተራ ጀርባ ከሚገኘው “ኳስ ሜዳ” ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ መሆኑም ታውቋል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና መሠረት በጉዳዮ ላይ ከበላይ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል “ለዛሬ 40ዎቹን ሰዎች እመረምራለሁ፣ ለወደፊቱ ግን እንዲህ ያለ ነገር የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሓላፊነት ስለሆነ ወደእኔ አትምጡ” የሚል መልዕክት በማስተላለፍ በከሰዐት በኋላው የሥራ መርሀ ግብር ለሰዎቹ ምርመራ ተደርጎላቸዋል።

LEAVE A REPLY