ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አራት የግል ትምህርት ቤቶች በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን እንዳያስተምሩ ታግደዋል ተባለ።
ትምህርት ቤቶቹ የአንድ ዓመት እገዳ የተላለፈባቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የሚያስከፍሉትን የአገልግሎት ክፍያ ከ50 እስከ 75 በመቶ እንዲያደርጉ ቢወሰንም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ከወላጆች ሙሉ ክፍያ በመቀበላቸው ነወ።
የከተማ መስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ያወጣውን ተደጋጋሚ መመሪያ በመጣሳቸው ፈቃዳቸው የታገደባቸው ትምህርት ቤቶች ፤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኙ ለምለምና ሮማን የሚባሉ ትምህርት ቤቶች፣ የካ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ስሪ ኤም አካዳሚና አራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ገነት መሰረተ ክርስቶስ መሆናቸው ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የትምህርትና ስልጠና ጥራት፣ ሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ፤ ” ትምህርት ቤቶች ከ50 እስከ 75 በመቶ እንዲያስከፍሉ የወጣውን መመሪያ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ አድርገዋል ፤ ሆኖም 21 ትምህርት ቤቶች ግን ከተፈቀድላቸው ውጪ ክፍያ በመጠየቃቸው፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ ማስተካከያ እንዲያደርጉ በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሰረት 17ቱ ያስተካከሉ ሲሆን ፤ እንዲታገዱ የተደረጉት 4 ትምህርት ቤቶች ግን ለማስተካከል ፈቃደኛ አልሆኑም” ሲሉ በጉዳዮ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ነገ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዮ የግል ትምህርት ቤቶች ወላጆችን መንግሥት ያወጣውን መመሪያ በሚጣረስ መልኩ ሙሉ ክፍያ እያስከፈሉ መሆኑን ቀደም ሲል በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።