ህወሓት የተሻለ ሐሳብ ያለውን ሲጎትት መኖሩን ነባር የድርጅቱ አመራር ተናገሩ

ህወሓት የተሻለ ሐሳብ ያለውን ሲጎትት መኖሩን ነባር የድርጅቱ አመራር ተናገሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ሚሊዮን አብርሃ ህወሓት የተሻለ ሐሳብ ይዞ የሚመጣን ሰወ ወደኋላ የማስቀረት አባዜው የጀመረው ዛሬ አይደለም ሲሉ የድርጅቱን አብሮ የኖረ ባህሪይ አጋልጠዋል።

በዚህን መሠሉ የህወሓት ተንኮል ክልሉን ብሎም አገርን መለወጥ የሚችሉ፣ በትግሉ ውስጥም ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ወጣቶች ከድርጅቱ በጊዜ ሂደት እየተንጠባጠቡ ለመውጣት መገደዳቸውን የጠቆሙት  ነባር ታጋይ፤ እርሳቸውም  ከድርጅቱ እንዲለቁ ያደረጋቸው፣ ለሐሳብ ልዩነት ቦታ አለመስጠቱና ዘመኑ ከሚፈልገው ለውጥ ጋር ለመሄድ ፍላጎት ያለመኖሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በህወሓት ውስጥ ልዩነቶችን እስከ መጨረሻው ይዞ መቆየት እንደ ነውር የሚቆጠርበት ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት አቶ ሚሊዮን፤  አሁን በህወሓት ሥም እየተንቀሳቀሱ ያሉ ጥቂት ቡድኖች የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በነፃነትና በትብብር እንዳይሠራ በማድረግ ላይ ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል።
“ህወሓት የክልሉን ሕዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመፍታት ይልቅ የብሽሽቅ ፖለቲካን በማራመድ ሕዝቡ ሌሎች ወንድሞቹን እንዲጠላ እያደረጉ ነው። የትግራይ ሕዝብ ከመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በፍቅርና በሰላም  የኖረ ቢሆንም፤ አሁን ግን አብዛኛው ሕዝብ ጥቂት የህወሓት ቡድኖች በሚፈጥሩት ፕሮፓጋንዳ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል፤ በዚህም ወጣቱ ከልማት ይልቅ ለጦርነት ልቡን በማነሳሳት ወደ ጥፋት የሚገፋፋ ሆኗል” ሲሉም ህወሓት የትግራይ ሕዝብን ለጥፋት እያነሳሳበት ያለውን መንገድ ተችቷል።
”ሃይማኖትና ሕዝብ አንድ አይደለም፤ ፖለቲካና ሕዝብም አንድ አይሆኑም” የሚሉት አቶ ሚሊዮን” ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ የተለያዩ መሆናቸውን አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል። ህወሓት በሐሳብ ልዩነት ሳይሆን በንትርክና በሹኩቻ በመምራት የትግራይን ሕዝብ ከልማትና ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ወደኋላ ያስቀረ ድርጅት  ነው ” ብለዋል።
ህወሓት አገር በሚያስተዳድርበት ጊዜም የትግራይ ሕዝብ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ የሆነለት እንዳልነበር፣ የቀድሞ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር በዚህም እንደ ሌሎች ሕዝቦች ለውጡን ይፈልገው እንደነበር ያስታወሱት የቀድሞ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር፤ ለውጥ ፈላጊው የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን ህወሓትን ከትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ለማንሳት የጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል መክረዋል።

LEAVE A REPLY