ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ማንኛውም ሰው ከቤቱ ውጭ ሲንቀሳቀስ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን የሚያስገድድ መመሪያ መውጣቱ ይፋ ሆነ።
ቀደም ሲል የሕዝብ ትራንስፖርት ሲጠቀሙ፣ ለመጠቀም ሰልፍ ሲይዙ፣ እንዲሁም በተለያዩ ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች ነበር ማስክ ማድረግ አስገዳጅ ሆኖ የቆየው።
ዛሬ ይፋ የሆነው አዲስ መመሪያ ግን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እየተስፋፋ በመሆኑ፣ ህጎችን ለማጥበቅ እንዳስገደደ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር የሚኒስትር ኮሚቴ አባል እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢተ ሕግ የሆኑት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።
በማሻሻያው መሠረት ከዛሬ ጀምሮ ማንኛውም ሰው ከቤቱ ውጭ ሲንቀሳቀስ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን አስገዳጅ የሚያደርግ መመሪያ መፅደቁ ተሰምቷል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በተጨማሪ በአገር አቋራጭ ትራንስፖርት አጠቃቀም፣ በመንግሥት ሠራተኞች የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዐትን ጨምሮ የተለያዮ ማሻሻያዎችን አድርጓል።