ዮጵያ ነገ ዜና፡– በስደት ላይ የነበሩ 333 ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ዛሬ ከቤይሩት _ ሊባኖስ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደረጉ።
ተመላሾቹ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ጽዮን ተክሉን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ሰዎችን ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በብዛት የሚደረግ ዝውውር በእጅጉ እንዲገደብ፤ ዝውውሩ የግድ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በውሳኔ ቁጥር A/RES/73/195 ቢያፀድቅም፤ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ካላቸው የሥራ ባህሪ አንጻር በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሥራ በማቆማቸውና ለተለያዩ ችግሮች በመጋለጣቸው ወደ ሀገራቸው መመለስ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተነግሯል።
በዚህ መሠረት ዜጎቹ ክብራቸው ተጠብቆ ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ የሚመራ 11 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ከተቋቁመውና በሰላም ሚኒስቴር ከሚመራው ግብረ ሃይል ጋር በቅንጅት ሥራ መጀመሩን ተከትሎ በዛሬው እለት 333 ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ተደርገዋል።