አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን ዶናልድ ትራምፕ ይፋ አደረጉ

አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን ዶናልድ ትራምፕ ይፋ አደረጉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት እያቋረጠች ነው ሲሉ አስታወቁ።

ድርጅቱ ቻይናን ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጠያቂ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል በማለት የከሰሱት አወዛጋቢው ፕሬዝዳንት፤ “ቻይና የዓለም ጤና ድርጅትን ሙሉ በመሉ ትቆጣጠረዋለች” ሲሉም ዳግም ዓለም ዐቀፍ ድርጅቱን አብጠልጥለዋል።
 “ዛሬ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር ያለንን ግንኙነት እናቋርጣለን። እናደርግ የነበረውን ድጋፍ ወደሌሎች ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና በጎ አድራጊዎች እናዘዋውራን” ሲሉም ተደምጠዋል።
“ቻይና የ100 ሺኅ አሜሪካውያንን ሕይወት የቀጠፈ ወረርሽኝ ቀስቅሳለች፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዓለምን እንዲያሳስት ቻይና ጫና አሳድራለች” በማለት ሀገራቸው አሜሪካ ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧን ይፋ ያደረጉት ፕሬዝዳንቱ ፤ ተቋሙ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እየሠራ ያለውን ሥራ ደካማ ነው ሲሉ ተችተውታል።
በዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም የሚመራው የዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራት በበኩላቸው፣ ለወረርሽኙ የተሰጠውን ዓለም አቀፋዊ ምላሽ የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን ለማዋቀር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት ያቋረጠችው አሜሪካ ለዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ አገሮች ግንባር ቀደም ስትሆን ፤ ባለፈው ዓመት ከ400 ሚሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ለተቋሙ ለግሳለች።

LEAVE A REPLY