የኦሮሚያ ክልል አምንስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን ሪፖርት አልቀበለውም አለ

የኦሮሚያ ክልል አምንስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን ሪፖርት አልቀበለውም አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሰብኣዊ መብት ጥሰት አለ ሲል ያወጣውን ሪፖርት የኦሮሚያ ክልል ውድቅ አድርጎታል።

ክልላዊ መንግሥቱ ሪፖርቱን የተሳሳተ እንደሆነ ከመግለፁ ባሻገር የዓለም ዐቀፉን ተቋም እውነተኛ ብቃት አደጋ ላይ እንደሚጥለውም ገልጿል።
“አምኒስት ኢንተርናሽናል  ያወጣው ሪፖርት የተሳሳተ እና እውነታውን ያላረጋገጠ ነው” ያሉት  የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሓላፊ  አቶ ጌታቸው ባልቻ፤ “የቀረበው ሪፖርት መንግሥትን ከሚቃወሙ ቡድኖች ብቻ የቀረበ እና ወገንተኛ ስለሆነ መንግሥት ሪፖርቱን አይቀበለውም” ሲሉም የሰብኣዊ መብት ድርጅቱን መግለጫ ውድቅ አድርገውታል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በተለይም በምዕራብ ወለጋና ምስራቅ ወለጋ ከሚንቀሳቀሱ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በተያያዘ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ቢኖሩም በክልሉ ከመንግሥት ይልቅ የተደራጁ መንጋ ቡድኖች በንፁሃን ዜግች ላይ የፈጸሙት ግፍ የከፋ እንደሆነ በርካቶች ይናገራሉ።
በያዝነው ወር በወርሃ ጥቅምት ጽንፈኛ ብሔርተኛው ጃዋር መሐመድ “ተከብቢያለሁ” በማለት ለደጋፊዎቹ ባስተላለፈው የፍርኃት መልዕክት በሐረርና ድሬደዋ፣ በባሌና አሩሲ፣ በአምቦና በአዳማ ንፁሃን ዜጎች ብሔርና ሃይማኖታቸው እየተለየ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸውና ሕይወታቸውን ያጡት በመንጋ ቡድኖች መሆኑ አይዘነጋም።
እነዚህ የጥፋት ቡድኖችና መሪዎቻቸው ያደረሱት አይረሴ ጭፍጨፋ በአምንስቲ ሪፖርት ውስጥ የጥቃት አድራሾቹ እና የአደረጃጀት ይዘታቸው ተዘርዝሮ መገለፅ ነበረበት የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች እነዚህን ሁሉ ጥፋቶች ወደ ክልሉ ወይም ፌደራል መንግሥት መጠቅለሉ ተገቢ አይደለም ሲሉ ይገልፃሉ።
በሌላ በኩል አምነስቲ የሚመረምረው የሽምቅ ተጠቂዎችን እንቅስቃሴ አለመሆኑን የሚገልፁ አስተያየት ሰጪዎች የግለሰቡንም ሆነ የሸማቂዎችን ጥፋት መከታተልና ሕግ ፊት ማቅረብ የመንግስት ኃላፊነት እንጂ የአምነስቲ ጉዳይ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።

LEAVE A REPLY