በአዲስ አበባ አራት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

በአዲስ አበባ አራት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ተባለ።

ግንባታቸው አልቋል ተብለው ከተመረቁት የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ 3.3 ኪ.ሜ ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት ያለው ከአራብሳ ኮንዶሚኒየም—አያት ኮንዶሚኒየም፣ እንዲሁም 2.1 ኪ.ሜትርና 20 ሜትር ስፋት ያለው ከሲ.ኤም.ሲ—አያት  የተገነቡት መንገዶች ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል።
ከገርጂ— ኢትዮ ፓረንት ስኩል፣ እንዲሁም ከጅቡቲ ኤምባሲ— ሰሚት የተገነቡት መንገዶችም በተመሳሳይ በዛሬው የተጠናቀቁ መንገዶች ምረቃ ውስጥ ተከተዋል።
ዛሬ ከተመረቁት መንገዶች ውስጥ ሁለቱ መጋቢ መንገዶች ናቸው ያሉት ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ፤  የከተማ አስተዳደሩ ለትራንስፖርት ዘርፉ አማራጭ የሚፈጥሩና መኖሪያ አካባቢዎችን ከዋና መንገዶች ጋር የሚያገናኙ መጋቢ መንገዶች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በተመረቁት አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን በስልክ ለማነጋገር የሞከረው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢ ዋና ዋና መንገዶቹ ቢጠናቀቁም በርካታ ቦታዎች ላይ የግራና የቀኝ የእግረኛ መንገዶች ገና ያላለቁ መሆናቸውን መገንዘብ ችያለሁ ሲል ዘግቧል።
ብዙ ጊዜ መንግሥት ለፖለቲካ ትርፍ ሲል ዋና መንገዶችን እንዳጠናቀቀ ማስመረቁ የተለመደ መሆኑን ያስታወሱት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፤ መንገዶቹ ከተመረቁ በኋላ በጅምር ላይ የሚገኙት የእግረኛ መተላለፊያ ግራና ቀኝ መንገዶች አስታዋሽ አጥተው እንደሚቀሩ ገልፀዋል።
መጪው ጊዜ የክረምት ወር በመሆኑ እነዚህ ተቆፍረው የተተው መንገዶች ክብልስቶን ወይም ቴራዞ በፍጥነት ሳይለብሱ ከቀሩ አካባቢዎቹ ክፉኛ እንደሚጨቀዩና ነዋሪዎችም እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ እንደሚቸገሩ ነዋሪዎች ከወዲሁ ገልፀዋል።
ዊልቸር፣ ክራንች መሰል የድጋፍ ቁሳቁስ የሚጠቀሙ አካል ጉዳተኞችንና አቅመ ደካሞችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት ከዋና መንገድ በተጨማሪ የእግረኛ እኩል መንገዶችን  ግንባታ ማጠናቀቅ አለበት በማለት ለኢትዮጵያ ነገ የጠቆሙት የመዲናዋ ነዋሪዎች ዛሬ ላይ በጨረፍታ ለካሜራ እይታ እንዲበቁ የተደረጉት ጥቂትና የተመረጡ የእግረኛ መንገዶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY