ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዛሬ በተካሄደው በአዲስ ወግ ዌቢናር 2፤ “ፈጠራ በቀውስ ጊዜ” በሚል ርዕስ በተካሄደው የምሁራን ውይይት ላይ የኮቪድ-19ን ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ የመፍትኄ ሐሳብች ቀረቡ።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የታሪክ ምሁር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ወረርሽኙን ለመከላከል የተለያዩ የመፍትኄ ያሏቸውን አማራጮች በውይይቱ ላይ አቅርበዋል።
“መንፈሳዊ ጥንካሬ ለማግኘት ፀሎትን በማብዛት ፈጣሪን መማፀን” እና ማኅበራዊ መስተጋብሮችን ማቋረጥም ተገቢ መሆኑን ፕ/ር አበባው አያሌው አስረድተዋል።
በተለይ ደግሞ እንደ ሰርግ፣ እድርና ደቦ የመሳሰሉ ማኅበራዊ መስተጋብሮችን በወረርሽኝ ወቅት ማቋረጥ ተገቢና አስፈላጊ ነው ያሉት ባለሥልጣኑ፤ ስብስብ ያለባቸውን ማኀበራት ማቋረጥ፣ አካላዊና አካባቢያዊ ፅዳትን ማጠናከርም ተገቢ እንደሆነም በዝርዝር አስረድተዋል።
አሁን የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመግታት ከተለመዱና ነባራዊ አሰራሮች መውጣት ይገባል ያሉት በአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የአዕምሮ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ባርኮት ሚልኪያስ፤ ችግሮችን በመለየት በፍጥነት ወደ መፍትኄ መግባት አገሪቱ አሁን ካለችበት ችግር አኳያ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በወረርሽኝ ወቅት የተለየ ፈጠራ ባይኖር እንኳን ትንንሽ የሚባሉ ማሻሻያዎችን በማድረግ አጋዥ መፍትኄዎችን ማመላከትም ጥቅሙ የጎላ እንደሆነ ምሁራኑ በውይይቱ ላይ ተናግረዋል።
በወረርሽኝ ወቅት በተለይ ደግሞ ማህበራዊ ከለላ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ሃኪሙ ዶክተር ቢኒያም ወርቁ ናቸው።
እንደ እርሳቸው ገለፃ ወቅታዊው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተለይ እድሜያቸው የገፋና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ሰዎች ላይ ይበረታል።
በመሆኑም ለእነዚህ ሰዎች ልዩ ትኩረት በማድረግ ማህበራዊ ከለላ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
እንደ አጠቃላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል መሰረታዊ የባህሪ ለውጥና የመከላከል ጥረቶችን ይጠይቃል ተብሏል።