ግንቦት 2012
እንኳን በአንድ አገር ሕዝብ ውስጥና፣ እንኳን በአንድ ከተማ የፖሊስ ኃይል ውስጥ ይቅርና በአንድ ቤተሰብም ውስጥ ጻድቅና ኃጥእ፣ የፍትሕ ሰውና ወንጀለኛ ይወለዳሉ፤ ጥያቄው እነዚህን ሁኔታዎች እንዴት እናስተናግዳቸዋለን? ነው።
ከመጀመሪያው እንነሣ፡ አንድ መለዮውን የለበሰና የታጠቀ የከተማው (ሚኒአፖሊስ) ነጭ ፖሊስ አንድ ጥቁር ዜጋን በግፍ ገደለ፤ አንድ ዜጋን አንድ ዜጋ ገደለ፤ መለዮ የለበሰውና የታጠቀው ሕግ አስከባሪው ዜጋ ሰላማዊውን ሰው በግፍ ገደለው፤ እንዲያውም አራት ሕግ አስከባሪዎች ነበሩ፤ ደስ የሚለውና የኢትዮጵያ ሕዝብም ሊማረው የሚገባ የሚኒአፖሊስ ከተማ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ ሕዝብ በሙሉ መቆጣቱን ነው፤ ተቆጥቶና ሰላማዊ ሰልፍ በማድረጉ ገዳዮቹ ከሥራቸው ተሰናበቱ፤ ዋናው ገዳይ ታስሮ ክስ ተመሠረተበት።
የአሜሪካ ሕዝብ ነጭ በደለ፤ጥቁር ተበደለ ሳይል አንድ ዜጋ ተበደለ ብሎ ጮኸ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ዓይነት ኅብረትና ይህንን ዓይነት ቁጣ ማሳየት መማር ያስፈልገዋል፤ በደርግ አገዛዝ በአራት ኪሎ በአንድ ገዳይ ላይ፣ በአዲሱ ከተማ በራጉኤል አካባቢ የአዲስ አበባ ነዋሪ አሳይቷል፤ ግፍ ሲፈጸም ቁጣን መግለጽ ለሕጋዊነት በኅብረት መቆም የማኅበረሰቡን የመንፈስ ልዕልና ያሳያል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉን አጨንግፎ ወደንብረት ማቃጠልና ሰዎችን ወደመጉዳት ሲለወጥ መጀመሪያውኑ ግፍ ከሠራው ፖሊስ ጋር መተባበርና አብሮ በመንፈስ መውደቅ ነው፤ ወይም አንድ ወሮበላ ፖሊስን ተከትሎ እሱ የሠራውን ግፍ ማራባት ነው፤ ይህ ለማንም አይጠቅምም፤ ማኅበረሰቡን አያሻሽልም፤ ኑሮን አያቃናም፤ ከግፈኛው ጋር የመንፈስ ጉድጓድ ውስጥ ወድቆ ከግፈኛው እሻላለሁ ማለት ራስን ማታለል ነው፡፡