ታድለሽ || ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን

ታድለሽ || ወሰንሰገድ ገ/ኪዳን

…[ክፍል 2]
.
አንቺዬ
አጀብ ነው ምትሃት – አጃኢብ ነው ውበት
ምን ይሆን አፈሩ – የተቀመምሽበት?

አንቺዬ
አጀብ የሚያሰኘው – የውበትሽ ነገር- ተቀርፆ በውስጤ
አለምን ዘንግቶ – ለእምነቱ እንዳ’ደረ – በብርቱ ምሳጤ
እያብሰለሰለኝ – በሃሳብ ተሻግሬ – ርቄ እሄዳለሁ፤
የፈጣሪን ጥበብ – ባንቺ የተነሳ – መመርመር ይዣለሁ፡፡

አንቺዬ፤
የብር ጉልላት- የሚመስለው ዐይንሽ – ክበበ ገፅሽ ላይ የሚያንፀባርቀው
ለአፍታ ሲወረወር – ልቦናን ሰቅዞ – አፍዝዞ ‘ ሚያስቀረው
ከባለ ዘንግ ጦር- በአያሌው የላቀ፤ ብርቱ ጦረኛ ነው፡፡

አንቺዬ፤
የመልከሽ መጠየም – ሐመልማልነትን – የተደንደረበበው
እንደሚያስተፈስህ – የወይን ጭማቂ – ሰዉ የሚያስጎመዠው
ከንፈርሽ ሲገለጥ – የሚፈለቀቀው – ችምችም ያለው ጥርስሽ
እንደአንበሳ ጋማ – የተዘናፈለው – ሐር መሳይ ፀጉርሽ
በሃሳቤ እየመጣ – እያነሆለለኝ – በጠራራ ፀሐይ – በቀን ያስቃዥኛል
ይብላኝልኝ ለእኔ – አንቺስ ታድለሻል!!

አንቺዬ፤
አጀብ ነው ምትሃት – አጃኢብ ነው ውበት
ምን ይሆን አፈሩ – የተቀመምሽበት?

አንቺዬ፤
አንዳንዴ ውበትሽ – ቀን በቀን ሲያስቃዠኝ- ስትመጭ በምናቤ
ይመሰለኛል በሃሳብ – ያለሽ አጠገቤ፡፡

እናም የውበትሽ ….
የውበትሽ ግርማ – የውበትሽ ሞገስ
ለእኔም ካባ ሆኖ – ይታየኛል ሥነግስ፡፡

እናም ይመስለኛል – በግርማ ሞገስሽ – በውበትሽን ፅጌ
አድርጌ አስባለሁ – እኔን እንደንጉስ – አንቺን እንደ እቴጌ፡፡

አንቺዬ
ይህ የምልሽ ሁሉ- ሐሰት እንዳይመልሽ – አመሰክራለሁ
ከእቴጌም እቴጌ – የእቴጌ እቴጌ ነሽ – በነፍሴ እምላለሁ፡፡
ታ….ድ….ለ….ሽ!!!!

LEAVE A REPLY