ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ቁጥጥር ውጪ የሆነች በምትመስለው በምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ወረዳ አራት የመንግሥት ሠራተኞች በታጣቂዎች መገደላቸው ተነገረ።
ዓርብ ዕለት የሸኔ አባላት ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በ10 የመንግሥት ሠራተኞች ላይ በፈጸሙት ጥቃት አራቱ ሲገደሉ፣ ሦስቱ የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸውና ቀሪዎቹ ሦስት ሰዎች ደግሞ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከጥቃቱ መትረፋቸው ታውቋል።
በዕለቱ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ለማከፋፈል ከተለያዩ ቢሮዎች የተወጣጣ ኮሚቴ፣ ” አሞማ ዴገሮ ” ወደ ተሰኘ ቀበሌ ተጉዞ እንደነበነር የተናገሩት የነጆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተፈራ “የመንግሥት ሠራተኞቹ ከሄዱበት ስፍራ ሥራቸውን ጨርሰው ሲመለሱ፤ ዋጋሪ ቡና ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ፣ ጸረ ሰላም በሆኑት የሸኔ ታጣቂዎች ተኩስ ተከፍቶበቸዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ሁኔታውን አስረድተዋል።
አንደኛው ሟች አብዲ አበራ የሚባል ሹፌር፣ ሁለተኛው የእንስሳት ሐኪም የነበረው ዳዊት ተርፋሳ፣ ባሕሩ አየለ እና እስራኤል መርዳሳ የሚባሉት ሟቾች ደግሞ የወረዳው ሚሊሻ አባላት እንደሆኑም ሓላፊው አስረድተዋል።
ኦነግ ሸኔም ሆነ ሌሎች ኃይላት ጥቃቱን በተመለከተ እስከሁን ምንም አይነት ምላሽ አልሰጡም።