በትግራይ “ቆራሪት” ከተማ በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ 45 ሰዎች ታሰሩ

በትግራይ “ቆራሪት” ከተማ በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ 45 ሰዎች ታሰሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ከተማ በትግራይ ክልል ምዕራብ ዞን፣ ቆራሪት በምትባል ከተማ በተቀሰቀሰ አዲስ ተቃውሞ ላለፉት ሁለት ቀናት መንገድ ዝግ ሆኖ መቆየቱ ተነገረ።

“የመሬት ካሳ ይከፈለን፣ ለከብቶች መዋያ ቦታ ይሰጠን፣ የመሬት ይዞታ ባለቤትነት ይረጋገጥልን፣ በከተማዋ የመሬት ጉዳይ ጽ/ቤት ይዋቀርልን” የሚሉ ጥያቄዎች ከሰልፈኞቹ ተሰምተዋል።
 የከተማዋ ነዋሪዎች ከሆኑት አቶ ደስታ ሃጎስ እና መምህር ገብረዋህድ ስለ ጉዳዮ ለቢቢሲ ሲያስረዱ “የመሬት ካሳው ጥያቄው ስለቆየብን ተቸግረናል፤ የምንበላው አጥተናል። መንግሥት ከገጠር ወደ ከተማ ሲያስገባን ቃሉን ይጠብቃል ብለን አምነን ነበረ፤ ነገር ግን እስካሁን ካሳው አልተሰጠንም፤ ካሳው ይሰጠን” ብለዋል።
እንዲህ ባሉ የኅብረተሰብ ጥያቄዎች የተጀመረው ሰላማዊ ሰልፍ  ሕዝብ እየተሰባሰበ ድንጋይ በመወራወር፣ መንገዶችን ወደ መዝጋት ማምራቱ የተነገረ ሲሆን፤ ከትናንት በስቲያ የተዘጋው መንገድም የተከፈተው ትናንት ማምሻውን መሆኑ ታውቋል።
 ከቆራሪት ከተማ ከአመራሮቹ አንዱ አቶ ኪዳነማሪያም አባይ፤ ከሕዝቡ የቀረበላቸውን ጥያቄ ትክክል መሆኑን አምነው፤ “አንዳንድ ሰዎች ግን የሕዝቡን ጥያቄ ተገን በማድረግ ድንጋይ እንዲወረወር፤ መንገድ እንዲዘጋና ሥራዎች እንዲስተጓጎሉ አድርገዋል። የሕዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየመለስን ነው” ብለዋል።
ያልተፈለገ አመጽና አድማ የፈጠሩ ሰዎችን ሥርዓት ማስያዝ ስላለብን የተወሰኑ ሰዎችን ወስደን ልንገስጽ እንፈልጋለን። የታሰሩ ሰዎችም ስላሉ እነሱንም መክረን እንመልሳቸዋለን ሲሉም ተናግረዋል።
አሁን ላይ በሥፍራው ተቃውሞውን ተከትሎ 45 ሰዎች እንደታሰሩ ቢነገርም፤ አመራሩ ግን ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም ሲሉ ተደምጠዋል።

LEAVE A REPLY