ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከሚሊኒየሙ ማግስት አንስቶ ታላላቅ መንግሥታዊና ሃይማኖታዊ፣ ባዛርና ክንሰርቶች ማካሄጃ ሆኖ የከረመው ሚሊኒየም አዳራሽ በዛሬው ዕለት የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ታማሚዎችን መቀበል ጀምሯል።
መንግሥት ከአንድ ወር በፊት ቫይረሱ እየተስፋፋ ከመጣ በአማራጭነት ሕመምተኞችን ማስተናገጃ ይሆናል በሚል በልዮ ሁኔታ በአልጋዎችና በሕክምና ቁሳቁሶች እንዲደራጅ የተደረገው ሚሊኒየም አዳራሽ ገና ከአሁኑ በኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች መያዝ ጀምሯል።
ዛሬ ሥራውን የጀመረው የአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 የህክምና ማዕከል 40 የጽኑ ሕሙማን መኝታዎች እና 1 ሺኅ ጽኑ ያልሆኑ ሕሙማን ታካሚዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ተነግሮለታል።
ጊዜያዊ የሕክምና ማዕከሉ የላቦራቶሪ፣ የመድኃኒት ቤት፣ የጤና ባለሙያዎች ልብስ መቀየሪያ፣ መታጠቢያዎችና ሌሎች ተጨማሪ ክፍሎች እንዲሟሉለት ተደርጓል።
ከማዕከሉ የጥበቃ ሠራተኞች ጀምሮ የሕክምና አገልግሎት ለሚሰጡ ነርሶችና ዶክተሮች ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ሠራተኞች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ፣ በተጨማሪም የአየር ሥርዓት ፍሰቱን ለማስተካከል የሚረዱ ዘመናዊ መሣሪያዎች እንዲገጠሙለት መድረጉንም ሰምተናል።