ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው “ማጎ ብሔራዊ ፓርክ” ውስጥ ስምንት ዝሆኖችን ከገደሉት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ በዝሆኖቹ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ መሆናቸው ተነገረ።
ዝሆኖቹን በመግደል ከተጠረጠሩትና ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ ቀደም ሲልበወረዳ አመራርነት ያገለገሉ ግለሰብ እንደሚገኙበት ታውቋል።
ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ዝሆኖቹ ውኃ ከሚጠጡበት ሥፍራ ሔደው በመመለስ ላይ በነበሩበት ወቅት፤ በታጣቂዎቹ በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው ማለፉንና የስምንቱም ዝሆኖች ጥርስ መወሰዱን የፓርኩ ጠባቂ አቶ ጋናቡል ቡልሚ ይፋ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህን ያህል ቁጥር ዝሆኖች ተገድለው እንደማይታወቅ የጠቆሙት የዜና ምንጮች፤ ከአምስት ዓመት በፊት በተደረገ ቆጠራ 175 ዝሆኖች መኖራቸው መረጋገጡንም ገልጸዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ስለፓርኩ ሲናገሩ፤ “ጆሮ ያለው የክልል አመራር ይስማ፡፡ እንስሳቱ ቢጠፉ ፓለቲካዊ አመራሩ የታሪክ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ዛሬ ያለው አመራር ወደፊት በታሪክ ፊት ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ሀገራዊ ሀብትና ለትውልድ የሚተርፍ ቅርስ እየጠፋ ነው፡፡” ማለታቸው አይዘነጋም።