ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ እስካሁን የተካሄደውን የምርመራ ሂደት ተከትሎ 49 የጤና ባለሙያዎችና 16 ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች (በድምሩ 65 የጤና ባለሙያዎች) የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
በሀገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ በግንቦት ወር ብቻ ከ1ሺኅ ሰዎች በላይ በቫይረሱ መያዛቸውንም በዋቢነት ጠቅሰዋል።
የኮቪድ 19 ቫይረስ ስርጭት ከማኅበረሰቡ ባሻገር በጤና ተቋማት በሚሠሩ ሐኪሞች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ላይ መከሰቱን የገለፁት ዶክተር ሊያ ታደስ፤ ባለሙያዎቹ በአብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የጤና ተቋማት የሚሠሩ ናቸው ብለዋል።
መንግሥት የጤና ተቋማት ሠራተኞችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከሚያደርገው ሥራ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ ራሱን በመጠበቅ የባለሙያዎቹን ጫና እንዲቀንስ የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ በተጨማሪም በማኅበረሰቡ የቫይረሱን ስርጭት የሚመጥን ጥንቃቄ አለመደረጉ እንደሚያሳስባቸውም አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ንክኪ አላቸው በሚል የተጠረጠሩ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረቦች የሆኑ 42 ፖሊሶች ኳራንቲ እንዲገቡ መደረጋቸውን ታማኝ ምንጮች ለኢትዮጵያ ነገ ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የቫይረሱ ተጠቂዎች በተገኙበት አብነትና ልደታ አካባቢ በሚገኘው ወረዳ 5 ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ አርባ ተጠርጣሪዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ የጸጥታ አባላቱም ለበሽታው ተጋላጭ መሆናቸው እየተነገረ ነው።
እንደ ታማኝ ምንጮች ገለጻ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ቫይረሱ ከተገኘባቸው የጸጥታ ባልደረቦቻቸው ጋር ቀጥታ ንክኪ አላቸው የተባሉ 42 ፖሊሶች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል።