ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኙ ቀን በቀን እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ፣ ቫይረሱ በእጅጉ በተስፋፋባት በአዲስ አበባ ሁለት ሆስፒታሎች ሊገነቡ መሆናቸው ተነገረ።
በከተማዋ በቫይረሱ የሚያዙ የታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፣ እንዲሁም ያሉት ሆስፒታሎች የማስተናገድ አቅማቸው ከታካሚው ቁጥር ጋር ባለመመጣጠኑ አገልግሎቱን ለማስፋፋት በንፍስ ስልክ ላፋቶ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ሁለት ሆስፒታሎችን መንግሥት ለማሠራት ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ሥድሥት የመንግሥት ሆስፒታሎች በርካታ ጤና ጣቢያዎች አሉ። የማስተናገድ አቅማቸውም ግን 1ሺኅ 557 ታካሚዎችን ብቻ ነው ተብሏል።
አዲስ የሚገነቡት ሁለቱ ሆስፒታሎች ሲጠናቀቁም 940 ታካሚዎችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖራቸው ይኖራቸዋል።
በሚገነቡት ሆስፒታሎች ዲዛይን ላይ የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ እና ሌሎች ጉዳይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ ኣካላት እየመከሩበት እንደሆነ አስታውቋል።
እነዚህ ሁለት ሆስፒታሎች የሚገነቡት ከወረርሽኙ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከሆነ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እንዲቻል በአነስተኛ ወጪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመር እንዳለበት የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች፤ በመንግሥት በኩል በዚህ ዙሪያ ግንባታው የሚጀመርበትና የሚያልቅበት ጊዜ አለመገለፁ፣ ሆስፒታሎቹ የረጅም ጊዜ ፕሮጀክት ተደርገው ከተያዙ ሕዝብን ከመታደግ አኳያ ከትርፉ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አሳስበዋል።