በፓርላማው የህወሓትና የሜቴክ ተጨማሪ የዘረፋ ገመናዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጋለጡ

በፓርላማው የህወሓትና የሜቴክ ተጨማሪ የዘረፋ ገመናዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጋለጡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤት ዛሬ በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ልዮ ስብሰባ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

“ህዳሴው ለሽያጭ፣ ለድርድር ቀርቧል የሚሉ አሉባልታዎችን እዚህ ማቅረብ ለምክር ቤቱ የሚመጥኑ ባይሆንም፤ ለምክር ቤቱ ክብር ስል ለማብራራት እሞክራለሁ በማለት አስገራሚ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬም የወያኔን ዘራፊነት በማስረጃ አስደግፈው አጋልጠዋል።
ሥድሥት ዓመት በዘገየው ግድብ 6 ቢሊዮን ዶላር ኢትዮጵያ አጥታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ግድቡን ስምንት ኮንትራት 6 ተቋራጮች እንደሚሠሩት አስታውሰው፣ አንዱ ተቋራጭ ከሥራ ቢዘገይ ለሌላው ተቋራጭ እንቅፋት እየሆነ ነው ብለዋል።
የግድቡን ፕሮጀክት ከጥንስሱ ጀምሮ የተወሰኑ ውሳኔዎችን ማጥናታቸውን እና በግድቡ ላይ ሜቴክ እንዲገባ መደረጉ ስህተት መሆኑን ተረድተናል በማለት ህወሓት መራሹ መንግሥት የዘረፋ ስልቱን ያመላከቱት ዐቢይ አሕመድ፤
 ከዚህ የተነሳ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎቹ እንደ አዲስ እንዲሠራ መደረጉን እና በመጪው ክረምት ግድቡ 4.9 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ እንደሚቻል አብራርተዋል።
ከለውጡ በኋላ ፕሮጅክቱ እንዴት እንደዳነ፤ የምክር ቤት አባላት ሄዳችሁ ማየት ትችላላችሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳሊኒ ሊሠራው የሚገባ ሥራ ተቀንሶ ለሜቴክ መሰጠቱ ግድቡን ቁልቁል ሲያንደረድረው ሰንብቷል ብለዋል።
ምርጫ ቦርድ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ምርጫ ማድረግ አልችልም የሚለው ሪፖርትን እንደሰማሁ  ከወ/ሪት ብርቱኳን ጋር ባልተለመደ መልኩ ጠንከር ያለ ንግግር አድርገናል ሲሉ በምርጫ መራዘም ዙሪያ ከምርጫ ቦርድ ጋር ልዮነት እንደነበራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።
ብልፅግና ምርጫው እንዲካሄድ ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው የተናገሩት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ብልጽግና ምርጫ የሚያስፈራው ፓርቲ እንዳልሆነ ለሁሉም ግልጽ ነው። ወ/ሪት ብርቱኳን፤ እስካሁን ከነበረው፣ በማንም መስፈርት የማያሳፍር ምርጫ ለማካሄድ ነው ሓላፊነት የተቀበልኩት። ከዚህ ውጪ የሆነ ምርጫ ይደረግ የሚሉ ከሆነ ሥራዬን እለቃለሁ። ምርጫ እንዲደረግ አታዙኝም፤ ብለው ስልኩ ተዘጋ” ሲሉም የነበረውን ሂደት አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ መንግሥት እየሠራው ስላለው ሥራ፣ ስለታገቱት የአማራ ክልል ሴት ተማሪዎች፣ ስለትግራይ ሕዝብና መንግሥት እንዲሁም ስለ ተለያዮ ጉዳዮች ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

LEAVE A REPLY