ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በተለያየ የውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ዶክተሮች ኢትዮጵያ ኮሮናን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ሊቀላቀሉ ነው ተባለ።
ለሀገራዊና ሕዝባዊ አገልግሎት ላይ ለመሠማራት የወሰኑት የሕክምና ባለሙያዎች አውሮፓ እና አውስትራሊያ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።
ከዚህ በፊት በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች፤ ባሉበት ሀገር ኮሮና የተገኘባቸውን ሰዎች በማከም የተሠማሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሠላማዊት ዳዊት አስታውሰዋል።
በውጭ የሚገኙት እነዚህ የሕክምና ባለሙያዎች ቫይረሱ የደረሰበትን ደረጃ እና የተለያዩ የጥናት ውጤቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለጤና ሚኒስቴር፣ ብሎም ሌሎች የመንግስት ተቋማት እየሰጡ መሆናቸውን የገለፁት ዳይሬክተሯ፤ አሁን ይህን ጥረት በአውሮፓ እና አውስትራሊያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞችም ተቀላቅለውታል ብለዋል።
ዶክተርቹ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሠዎች በማከም ተግባር ከተሰማሩ ኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው ጋር በሥራ አጋጣሚ ያገኟቸውን ልምዶች እንደሚለዋወጡም ተሰምቷል።
በተያያዘ ዜና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚረዳ የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው። ዳያስፖራዎቹ እስከ አሁን ከ140 ሚሊየን ብር በላይ መለገሳቸው ተረጋግጧል።
ከገንዘብ በተጨማሪ በትረስት ፈንድ በኩል ከሁለት ሳምንት በፊት 40 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የሕክምና ቁሳቁስም ድጋፍ አድርገዋል።