የሦስትዮሽ ድርድሩ አልሰመረም ሀገራቱ ዛሬም እየመከሩ ናቸው

የሦስትዮሽ ድርድሩ አልሰመረም ሀገራቱ ዛሬም እየመከሩ ናቸው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ለወራት ተቋርጦ የነበረው በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል የህዳሴው ግድብን በተመለከተ የሚደረገው ድርድር በደቡብ አፍሪካ፣ በአውሮፓ ሕብረትና በአሜሪካ ታዛቢነት ተጀምሯል። በአንዳንድ ነጥቦች ላይ አሁንም መግባባት አልተደረሰም ተብሏል።

በድርድሩ በታዛቢነት የሚሳተፉት አገራት ሚናን በተመለከተ ምን መሆን ይገባዋል? በሚለው ሐሳብ ላይ በተደራዳሪ አገራቱ መካከል መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።
ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው፣ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር የተራዘመ ድርድርና ውይይት ሲደረግበት የቆየው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመለከተው ድርድር መጀመሩን የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገልጿል።
ይህ በሦስቱ አገራት መካከል የሚደረገው ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌትና ዓመታዊ አለቃቅ ላይ ብቻ የተወሰነ እንደሚሆን ያመላከተው መግለጫ፤ ድርድሩ ማክሰኞ ሰኔ 2/2012 ዓ.ም በበይነ-መረብ የቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት ቀደም ሲል ተሳታፊ ከነበረችው አሜሪካ በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካናና የአውሮፓ ሕብረትን ጨምሮ በታዛቢነት በተገኙበት በአገራቱ የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ተካሂዷል።
ከወራት በኋላ በተካሄደው የመጀመሪያ ስብሰባ ተሳታፊ አገራቱ ስለድርድሩ የአካሄድ ሥነ ሥርዓት፣ ስለታዛቢዎችና ሌሎች ዋና ዋና ያልተቋጩ ጉዳዮችን በተመለከተ ተወያይተዋል።
በሌላ በኩል ተደራዳሪ አገራቱ ቁልፍ የድርድር ጉዳዮች ናቸው ያሏቸውን ሐሳቦች በዝርዝር አቅርበው፤ በቀጣይ ቀናት ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ ከስምምነት የደረሱ ሲሆን፣ ስምምነት ባልተደረሰበት የድርድሩ ታዛቢዎች ሚናን በሚመለከት ያለው ልዩነት ላይ መፍትኄ ለመስጠት ዛሬም በስብሰባው በስፋት እየተመከረበት ነው ተብሏል።
 “የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ዝግጁ ናት” ሲልም ድርድሩን እያካሄደ ያለው የውኃ፣ የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

LEAVE A REPLY