ከተቀበሩ በኋላ ኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ግለሰብ ጋር ንክኪ ያላቸው 52 ሰዎች ሰሜን...

ከተቀበሩ በኋላ ኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ግለሰብ ጋር ንክኪ ያላቸው 52 ሰዎች ሰሜን ሸዋ ማቆያ ገቡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ሕይወታቸው አልፎ ከተቀበሩ በኋላ አስቀድሞ በተደረገላቸው ምርመራ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን ተከትሎ የአንድ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ሰዎች በጅምላ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደረገ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ የተወለዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ በሥራ ቦታ በገጠማቸው አደጋ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ በተጨማሪነት የኮሮና ምርመራ ተደርጎላቸው የምርመራ ውጤቱ ሳይታወቅ ነበር ሕይወታቸው ያለፈው።
ይህን ተከትሎ ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆች አስከሬኑን ግንቦት 29/2012 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው እንሳሮ በመውሰድ ፤ በዚያው ዕለት ካራምባ ቀበሌ ጥቁር ዱር ሚካኤል የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ቢፈጸምም፣ በቀጣዩ ቀን ከግለሰቡ የተወሰደው ናሙና ቫይረሱ እንዳለባቸው ማረጋገጡ ተሰምቷል።
ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ወደለይቶ ማቆያ ከማስገባት በተጨማሪ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች ራሳቸውን ለይተው እስከ 14 ቀናት ድረስ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ መመሪያ ተላልፏል ያሉት የወረዳው ጤና ሓላፊ ወ/ሮ ፀዳለ ሰሙ ንጉሥ፤ ውጤቱ እሑዱ 10 ሰዓት አካባቢ እንደደረሳቸው 52 ሰዎችን በመለየት ምሽቱን ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY