ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ በወንዟ እና በግዛቷ ግድብ የመሥራት እና ኃይል የማመንጨት ሙሉ መብት እንዳላት የሱዳን ባለሥልጣናት ተናገሩ።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የውኃ እና መስኖ ሚኒስትሩ፣ እንዲሁም የሀገሪቱ ብሔራዊ ኡማ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት፤ በሀገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የቀጥታ ስርጭት ላይ ቀርበው ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከፍተኛ የሀገሪቱ የሥራ ሓላፊዎች ሱዳን ግድቡን አስመልክቶ የግብጽ እና ኢትዮጵያ አሸማጋይ ሣትሆን እንደ አንድ ቁልፍ የጉዳዩ ባለቤት ናት ካሉ በኋላ፤ ሱዳን ከኢትዮጵያ ከምትጋራው ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገነባው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት አያጠያይቅም ሲሉም እምነታቸውን ገልጸዋል።
ግድቡ ዓመቱን ሙሉ የተረጋጋ የውኃ ፍሰት እንዲኖር፣ ተደጋጋሚ ጎርፍ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ከመቀነስ ባሻገር ሱዳን በአባይ ውሃ ላይ ያላትን ጥቅም በዘላቄታዊነት ያስጠብቃል ያሉት ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ፤ የሦሥትዮሽ ውይይቱ እና ድርድሩ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በሚያሰፍን መልኩ ከስምምነት መደረስ እንደሚገባውም አብራርተዋል።
በዓለም አዐቀፍ የውኃ ሕጎች፣ አልያም በ2015ቱ የመርሆ ስምምነት ስለ ግድቡ የሚደረገው ወይይት መቋጫውን እንዲያገኝ የሱዳን ፍላጎት ነው እንደሆነ የገለፁት የሱዳን ባለሥልጣናት፤ ኢትዮጵያ ኃይል እያመነጨች ሱዳን ደግሞ ከሚኖረው የግድቡ የተረጋጋ የውሃ ፍሰት በብዙ መልኩ ተጠቃሚ ትሆናለች ሲሉም ገልጸዋል።
“ሱዳን አንዴ ከኢትዮያ ጎን ሌላ ግዜ ደግሞ ከግብጽ ጎን እንደሆነች ይነገራል ይሄ ስህተት ነው” ያሉት የውሃ እና መስኖ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ያሲር አባስ ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ሀገራቸው እንደምትደግፍና ኢትዮጵያም ያንን ለማድረግ ማንንም ማስፈቀድ እንደማይጠበቅባት፣ መብቷም ጭምር መሆኑን በይፋ አረጋግጠዋል።