ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዛሬ ስብሰባ የተቀመጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫ ለማራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በአብላጫ ድምጽ አፀደቀ።
ቀጣዮንና ሥድሥተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ለማራዘም የቀረበ የውሳኔ ሐሳብ ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ባደረገው ውይይት የውሳኔ ሐሳቡን ተቀብሎ በ114 ድጋፍ፣ በአራት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ አፅድቆታል።
ብሔራዊ ምርጫን ለማራዘም፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ስጋት ሆኖ እስከ ቀጠለበት ድረስ የሁሉም ምክር ቤቶች ሥልጣን እንዲቀጥል ውሳኔ አሳልፏል።
በተጨማሪም ወረርሽኙ ስጋት አለመሆኑን ዓለም ዐቀፍ የጤና ተቋማት ካረጋገጡ በኋላ ፤ የሐዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይህንኑ ውሳኔ ካጸደቀ በኋላ፤ ከ9 ወር እስከ አንድ ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ ምርጫ ይካሄድ ከሚል ውሳኔ ላይ ተደርሷል።