ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ጉባዔ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ውስጥ ራሳቸውን ሊቃነ ጳጳሳት ብለው የሰየሙትን አካላት ሥልጣነ ክህነት ማገዱ ተሰማ።
ግለሰቦቹ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት፣ ቆጋ ኪዳነ ምህረት ገዳም ነው ራሳቸውን የሾሙት።
በጉባኤው ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የጉዳዩን ዝርዝር ሂደት ለቅዱስ ሲኖዶሱ አቅርበዋል። ቅዱስ ሲኖዶስም ጉዳዮን በጥልቀት ከመረመረ በኋላ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ግለሰቦቹ የሄዱበት ርቀት ከሕግ አግባብ ውጭ ነው ሲል ከስምምነት ላይ ደርሷል።
ይህን ተከትሎም ግለሰቦቹ በማናቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምንም ዓይነት የክህነት አገልግሎት እንዳይፈጽሙ፣ ሥልጣነ ክህነታቸው እንዲያዝ ሲኖዶሱ ውሳኔ አሳልፏል።
ከውሳኔው በተጨማሪ ለጉዳዩ የመጨረሻ እልባት ለመስጠትም ግለሰቦቹ ቀርበው እንዲጠየቁና መልስ እንዲሰጡበት የንስሐ መንገድ ያመቻቸላቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ለዚህም ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ ሰይሟል።
ሲኖዶሱ ጉባኤውን ቢያጠናቅቅም ቋሚ ሲኖዶሱ ግን ለዚህ ድፍረት ተባባሪ የሆኑትን “የቅብዐት” አራማጆችን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ ሀገረ ስብከት ድረስ የተሰገሰጉትን አጥንቶ ሊደርስባቸውና መስመርም ሊያሲዛቸው ይገባል ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።