ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ በተደረገው 6 ሺኅ 630 የላብራቶሪ ምርመራ 164 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን ተከትሎ፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2ሺኅ 670 መድረሱ ታውቋል።
እንደ ጤና ሚኒስቴር መግለጫ ዛሬ ቫይረሱ የተገኘባቸው 117 ወንዶች እና 47 ሴቶች፣ የእድሜ ክልላቸውም ከ1 እስከ 92 ዓመት ውስጥ የሚገኝ ነው።
ቫይረሱ በምርመራ የተረጋገጠባቸው 104 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 26 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 22 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 4 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 4 ሰዎች ከደቡብ ክልል፣ 2 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል ሲሆኑ፤ ከሐረሪ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችም አንድ፣ አንድ ሰው እንደተገኘባቸው ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አምስት ኢትዮጵያዊያን (አራት ከአዲስ አበባ፣ አንድ ከሶማሊ ክልል) በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ መሞታቸውን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ በኢትዮጵያ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 40 መድረሱንም አስታውቋል።