ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትን ተከትሎ የሚሞቱ ሰዎች በጠቅላላ የአስከሬን ምርመራ እንዲደረግላቸው የሚያስገድደው አሠራር ከፍተኛ የሆነ መጓተት እንዳለበት ተነገረ።
በተለይም ባለፉት ሁለት ሳምንታት በርካታ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ (አንዳንዶቹ ደም ሰጥተው ውጤት ሳይደርስ ሕይወታቸው ያለፈ ነው) የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው በላብራቶሪ መረጋገጡ አሠራሩ በዋና መመሪያነት እንዲቀመጥ አድርጎታል።
የአስከሬን ምርመራ መደረጉ ለሁሉም ህብረተሰብ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ባይካድም አንድ ሰው ሞቶ አስከሬኑ ለምርመራ ማረጋገጫ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ በምንም ይሙት በምን ውጤት ለማግኘት ከአራት ቀን እስከ አንድ ሳምንት መጠበቅ መደበኛ አሠራር እየሆነ መጥቷል ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ።
ይህንን የሕዝብ እሮሮና ያለውን መጓተት በደንብ ተገንዝቢያለሁ ያለው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በበኩሉ፤ ምርመራው እንዲፈጥን ሌሎች ዘዴዎችም ካሉ እነርሱን ለመጠቀም ከሙያተኞችና ጉዳዮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከርኩ ስለሆነ ኅብረተሰቡ ትንሽ ሊታገሰኝ ይገባል ብሏል።