ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ብልጽግና ፓርቲ ከህወሓት ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ስላልቻሉ ምርጫ ቦርድ ሁለት ኦዲተሮችን ሾሚያለሁ ብሏል።
የኢሕአዴግ የመፍረስ ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ብልጽግናና ህወሓት ሀብት ክፍፍልን የሚቆጣጠር አንድ የጋራ አጣሪ እንዲመርጡ ለማስቻል የተደረገው ጥረትን ተከትሎ ሁለቱም ፓርቲዎች አንድ፣ አንድ ኦዲተር እንዲወክሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የንብረት ማጣራቱ ሥራውን እንዲያካሂዱ የተመረጡት ድርጅቶች እነማን እንደሆኑ እስካሁን ምርጫ ቦርድ አላሳወቀም። ነገር ግን ሥራቸውን በጋራ የሚያከናውኑበትን ዝርዝር ጉዳዮችን በማዘጋጀት ለቦርዱ እንሚያቀርቡ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
ብልፅግና ከተመሰረተ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኢሕአዴግ እንዲፈርስ፣ የሦስቱ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ወራሽ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በስድስት ወር ውስጥ የንብረት ክፍፍላቸውን አጠናቀው እንዲያቀርቡ ቀደም ሲል ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
በውሳኔው መሰረት ብልፅግና ከግንባሩ ሀብት ሦስት አራተኛውን፣ ህወሓት ደግሞ አንድ አራተኛውን እንዲወስዱ ቦርዱ ቢወስንም፤ የብልጽግና ፓርቲ የንብረት ክፍፍሉ እያንዳንዱ ፓርቲ በተናጠል በነበረው የአባላት ብዛት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል የሚል አቤቱታ እንዳቀረበ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
ይሁን እንጂ ቦርዱ የሃብት ክፍፍሉ የፓርቲው ሕገ ደንብ “ሁሉም ፓርቲዎች በግንባሩ የጋራ ንብረት እኩል የመጠቀም መብት አላቸው” በማለት ያስቀመጠውን መመሪያ መሰረት በማድረግ ውሳኔ መስጠቱን ጠቁሞ፤ ሆኖም ብልጽግና ከዚህ የተለየ ውጤት ሊያስከትል የሚችል ማስረጃ ወይም ሰነድ ካለው ለአጣሪው ማቅረብ እንደሚችል አስታውቋል።