ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ህወሓት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና ለአፍሪካ ኅብረት ሰሞኑን ያቀረበው ጥሪ “ጩኸቴን ቀሙኝ” ዓይነት መሆኑን ዶ/ር አረጋዊ በርሄ አስታወቁ።
እንዲህ ያለ ግፍ፤ አፈና እና ግድያ ያለው ህወሓት በመሸገበት ትግራይ ክልል ነው ሲሉ የተናገሩት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ ክሱ መሰረተ ቢስ እና ከእውነት የራቀ ውንጀላ ነው በማለት አጣጥለውታል።
“አምባገነናዊ ስርዓት ያለው በትግራይ እንጂ እንደ ሀገር በዚህ ልክ የሚገለጽ የመንግሥት ስርዓት የለም” ያሉት የቀድሞ የህወሓት መስራችና ሊቀ መንበር አረጋዊ በርሄ፤ በኮቪድ-19 ሳቢያ መካሄድ ያልቻለው 6ኛው ሀገር ዐቀፍ ምርጫ መራዘም ህጋዊ አግባብን የተከተለ ቢሆንም፣ የትግራይ ክልል መንግሥት ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ባቀረበው ጥሪ ሀቁን ለማሳሳት ሞክሯል ብለዋል።
“ኢሕአዴግን አፍርሶ በብልፅግና ፓርቲ የመተካቱ ሒደት ደም አፋሳሽ ያልሆነ የመንግሥት ግልበጣ ሊባል ይችላል” የሚለውን በደብዳቤ ውስጥ የተካተተውንም ሐሳብ በተመለከተ፤ “እነዚህ መገለጫዎች ያሉት አሁን በሥራ ላይ ባለው መንግሥት ሳይሆን በራሱ በህወሓት አስተዳደር ነው ። ለዚህም ከሰሞኑ በክልሉ የተከሰቱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው” በማለት ያላቸውን አቋም አሳይተዋል።