ጃዋር መሐመድ አሜሪካዊነቱን እንዳልቀየረ አረጋግጫለሁ ሲሉ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተናገሩ

ጃዋር መሐመድ አሜሪካዊነቱን እንዳልቀየረ አረጋግጫለሁ ሲሉ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተናገሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ጠንካራ በመሆኑ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ይቋቋም የሚለውን ሐሳብ አልደግፍም ሲሉ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ገለፁ።

አሁን በሀገሪቱ እየታየ ያለው የእኔ ብቻ የፖለቲካ አካሄድ ለሀገሪቷ ብሎም ለሕዝቦቿ አይጠቅምም ያሉት የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ ዛሬ በገበያ ላይ ከዋለው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በተለያዮ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
“ህወሓትን በተመለከተ የሚያሳፍር ነገር ነው እየሰማሁ ያለሁት። ልምድ እንዳለው ፖለቲከኛ ሆነው አላገኘኋቸውም፤ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳትና በሰጥቶ መቀበል መርህ በመዳኘት አሁን እየፈጠሩት ያለውን ጡዘት ማርገብ ይጠበቅባቸው ነበር።” ሲሉ ፓርቲው ሀገሪቱን ካለችበት ለውጥና መረጋጋት ወደ ብጥብጥና ረብሻ ሊወስዳት እንደሚሻ አስረድተዋል።
በአሁኑ ሰዐት ሀገሪቱ ውስጥ የተለያዮ ፖለቲካዊና ሕዝባዊ አመጾችን ለማነሳሳት እየጣረ የሚገኘው ጃዋር መሐመድ ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንደሌለው እርግጠኛ መሆናቸውን የጠቆሙት ፕ/ር በየነ፤ ” እኛ የአቶ ጀዋርን ወደ ኦ.ፌ.ኮ መቀላቀል የሰማነው ዘግይተን ነው። በእርግጥ መድረክ ውስጥ አባል የሚሆኑት ፓርቲዎች ናቸው፤ ግለሰቦች አይደሉም።  አንድ ፓርቲ ግለሰብን አባል አድርጎ ሲቀበል የፓርቲው ውሳኔ ነው እንጂ ሌሎቹን የጥምረቱን ፓርቲ አባላት የማማከርም ሆነ የማሳወቅ ግዴታ የለበትም።
ይሁን እንጂ የአቶ ጃዋር ጉዳይ እየጎላ ሲመጣና የዜግነቱ ጉዳይ እየተነሳ መከራከሪያ ሲሆን መድረክን ለማዳን ስል ጉዳዩን ለማጣራት ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ሄጄ ነበር። በኤምባሲው የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊውን በአነጋገርኩበት ወቅትም ጀዋር የአሜሪካ ዜግነት እንዳለው በግልጽ ነግሮኛል። ስለዚህም ጀዋር የውጭ ዜጋ ነው።” ብለዋል።
“አንድ የውጭ ዜግነት ያለው ሰው በሌላው አገር ፖለቲካ ውስጥ ግብቶ እንቅስቃሴ ማድረጉ አግባብ አለመሆኑን ስለምረዳ የሚመለከተው አካል አንዳች ውሳኔ እንዲያሳልፍ በግልጽ ተናግሬ ነበር” የሚሉት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ መንግሥት ለጉዳዩ በቂ ትኩረት የሰጠው አይመስለኝም፤ እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም ሲሉ በበላይ አካላት ዘንድ ቸልተኝነት መኖሩን አብራርተዋል።
ኦፌኮ፤ ሲአንና አረና ምርጫ መካሄድ አለበት ካልሆነም ብሔራዊ አንድነት መንግሥት መቋቋም አለበት የሚል አቋም እያራመዱ ቢሆንም  እርሳቸው የሚመሩት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ እና የአፋር ህዝቦች ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የምርጫውን መራዘምን እንደሚደግፉም ገልጸዋል።

LEAVE A REPLY