ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የጆርጅ ፍሎይድ መገደልን ተከትሎ የተነሳው ሕዝባዊ አመጽ ሳይበርድ ሌላ ጥቁር አሜሪካዊ በአትላንታ ከተማ በነጭ ፖሊስ መገደሉ ታወቀ።
በአትላንታ በሚገኘው ዌንዲስ ሬስቶራንት በር ላይ መኪናው ውስጥ ተኝቶ የነበረው ጥቁር አሜሪካዊ በፖሊስ መገደሉን ተከትሎ የአትላንታ ፖሊስ ኃላፊ ሥራቸውን መልቀቃቸውም እየተነገረ ነው።
ራይሻርድ ብሩክስ የተሰኘው የ27 ዓመት ጥቁር አሜሪካዊ፤ በፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት የተገደለው አርብ ዕለት መሆኑን ባለስልጣናት ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ይህን ግድያ ተከትሎ የከተማዋ ፖሊስ ሓላፊ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን የአትላንታ ከንቲባ ኬይሻ ላንስ ቦተምስ እንዳሳወቁት ገልጸዋል።
ቅዳሜ ምሽትም ኢንተርስቴት-75 የተባለው የከተማውን ትልቁን አውራ ጎዳና የዘጉትና ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ አሜሪካውያን፤ ራይሻርድ ብሩክስ የተገደለበትን ዌንዲስ ሬስቶራንትም በእሳት አንድደውታል።
ሥራቸውን የለቀቁት ኤሪካ ሺልድስ በፖሊስ ሓላፊነት ለአራት ዓመታት፣ እንዲሁም በተራ ፖሊስነት ለሃያ ዓመታት ያህል ማገልገላቸውን የተናገሩት ከንቲባዋ፤ ግለሰቧ ከፖሊስ ሓላፊነቷ ብትነሳም በሌላ የሥራ ድርሻ እንደምትሳተፍ እና በተጨማሪም ራይሻርድ ብሩክስን የገደለው ፖሊስም ከሥራ እንዲባረር ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል።
ግድያውን አስመልክቶ የጆርጂያ የምርመራ ቢሮ ከዌንዲስ ሬስቶራንት ያገኘውን እንዲሁም በአይን እማኞች አማካኝነት የተቀረፁትን ቪዲዮዎች እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል።
ራይሻርድ ብሩክስ ከሬስቶራንቱ ውጭ መኪናው ውስጥ ተኝቶ የነበረ ሲሆን ፣ ከኋላውም ለነበረው መኪና መተላለፊያ ዘግቷልም በሚል ፖሊስ ጋር መደወሉን የጠቆመው ፖሊስ፤ ራይሻርድ ብሩክስ መጠጥ ከሚፈቀደው ውጭ በላይ ጠጥቶ እንደነበርና በቁጥጥር ስር ለማዋልም ሲሞክሩ እምቢተኝነቱን አሳይቷል ሲል ገልጿል።
የምርመራ ቢሮው ከሬስቶራንቱ አገኘሁት ባለው ቪዲዮ ፖሊሶች ራይሻርድ ብሩክስን ሲያሯሩጡት እንደነበር፣ ብሩክስም የማደንዘዣ መሳያ (ቴዘር) በአንደኛው ፖሊስ ላይ መደገኑና ፖሊሱም በጥቁር አሜሪካዊው ላይ ሽጉጥ እንደተኮሰበትም ተረድቻለሁ ብሏል።
በአንጻሩ ከአይን እማኝ የተገኘው ቪዲዮ፤ ዌንዲስ ሬስቶራንት ውጭ ላይ ሁለት ፖሊሶች ጥቁር አሜሪካዊውን ከላይ ተጭነውት እንደነበርና ከእነርሱ ነፃ ለመውጣት ሲታገል እንደነበር፣ ድንገትም ከአንደኛው ፖሊስ የማደንዘዣ መሳሪያውን ነጥቆ ሲሮጥ፣ ሌላኛው ፖሊስ ብሩክስንና ሁለት አሜሪካውያን ሲያ ደነዝዛቸው፣ እንዲሁም የጥይት ድምፅ ሲሰማና ብሩክስን ሲወድቅ እንደሚያሳይ መረጃዎች ይጠቁማሉ።