ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ታይቶ የነበረው የደም እጥረት አሁን ላይ መፈታቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ባንክ ገለፀ።
“ደም በመለገስ ዓለማችንን የበለጠ ጤናማ ያድርጉ” በሚል መሪ ቃል ዓለም ዐቀፉ የደም ለጋሾች ቀን በዛሬው ዕለት ታስቦ ውሏል።
ሰኔ 7 ቀን የሚከበረው የዓለም ደም ለጋሾች ቀን ዘንድሮም ኮሮና ባስከተለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ተሰባስቦ ማክበር ባይቻልም በዓሉ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ “ደም በመለገስ ዓለማችንን የበለጠ ጤናማ ያድርጉ” በሚል በተለያዮ ሥነ ሥርዓቶችና የደም ልገሳ ሂደቶች እየተከበረ ነው።
“በዓሉን በጋራ ማክብር ባይቻለም ለሁሉም በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾቻችን ባሉበት በደም ተጠቃሚ ታካሚዎቻችን ስም ምስጋናችንን እናቀርባለን” ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት፤ ወቅቱ ባስከተለው ችግር ምክንያት በጎ ፍቃደኞች ደም ለመለገስ ወደ ደም ባንክም ሆነ ወደ ሕክምና ተቋማት መምጣት ባለመቻላቸው በአገር ዐቀፍ ደረጃ የደም እጥርት ተከሰቶ ነበር ሲል አስታውሷል።
በተላላፈው ሀገራዊ ጥሪ በጎ ፈቃደኞች ደም በመለገስ ተከስቶ የነበረው የደም እጥረት መፈታቱን እና በአሁኑ ውቅትም በሁሉም ደም ባንኮች በቂ የሆነ የደም ክምችት እንደሚገኝም ተቋሙ አረጋግጧል።