የሀገር ሽማግሌው ቡድን ከመቀሌ መልስ በኦሮሚያ ወደሚገኘው የሸኔ ታጣቂ ፊቱን ያዞራል

የሀገር ሽማግሌው ቡድን ከመቀሌ መልስ በኦሮሚያ ወደሚገኘው የሸኔ ታጣቂ ፊቱን ያዞራል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና–  በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መስተዳደር መካከል ያለውን አለመግባባት በሽምግልና መፍትኄ እንዲያገኝ ለማገዝ ዛሬ  መቀለ የገባው የሽምግልና ቡድን በቀጣይ ይህንን ጥረቱን በኦሮሚያ ክልል እንደሚደግመው ተነገረ።

ለረጅም ጊዜ ግጭቶችና የሰላም መደፍረስ እንዳጋጠመ በሚነገርለት የምዕራብ ኦሮሚያ እካባቢዎች የሀገር ሽማግሌ ቡድኑ በመንቀሳቀስ ሰላም እንዲወርድ እንደሚጥርም ተሰምቷል።
ከለውጡ ማግስትና ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አለመግባባት ከጊዜ እየተካረረ ሄዶ፣ ከኢሕአዴግ መክሰም በኋላ የነበራቸው ግንኙነት ከመቋረጡ ባሻገር የለየለት ውዝግብ ውስ መግባታቸው ይታወሳል።
ችግሩ ያሳሰባቸው የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብ ወደ ትግራይ ዛሬ ማለዳ ትግራይ የገቡ ሲሆን፤ የቡድኑ አባላት ከህወሓት ሹማምንት ጋር በጉዳዮ ላይ ከመከረ በኋላ፤ ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ እንደሚመለስ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ መስዑድ አደም ተናግረዋል።
የሽምግልና ቡድኑ በመቀሌ በሚያደርገው ውይይት፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው አለመግባባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ ስለሄደ ፣ ችግሩ እንዲፈታ ፣ ብሎም መቀራረብና መነጋገር አስስፈጊ መሆኑን ያስረዳል ተብሏል።
 የሽምግልና ቡድኑ በሁለቱ ወገኖች ፖለቲካዊ አመለካከት የሚያነሳው ነገር እንደሌለ የጠቆሙት አቶ መስዑድ መግባባትን በመፍጠር አገራዊ ሓላፊነትን ለመወጣት እንደሚጥሩ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባሩ እንደሆነ አስረድተዋል።
“እንደ ሃይማኖት አባትም እንደ አገር ሽማግሌም በዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋገሩ እንላለን፤ ከዚያም በሚደረጉ ውይይቶችና በሚደረጉ ድርድሮች ላይ መፍትኄዎች ይመጣሉ ብለን እናስባለን” ያሉት የሕዝብ ግንኙነቱ፤
እንደ ሽምግልና ቡድኑ እምነት ለሚታየው አለመግባባት ዋነኛው ችግር ያጋጠሙ ቅራኔዎችን ተቀራርቦ መነጋገር አለመቻል ነው ብሎ እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
በቀጣይ ይህ የሽምግልና ቡድን ሰላም በራቀው ምዕራብ ወለጋና ምስራቅ ወለጋ ከሚንቀሳቀሰው የሸኔ ጦር እና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር ስምምነት ስለሚፈጠርበት ሁኔታ ለመወያየትና እርቅ ለመፍጠር እቅድ መያዙ ታውቋል።
በአማራ ክልል የቅማንት፣ የራያና የወልቃይት ጉዳዮችንም በሰላም ለመቋጨት የሽምግልና ቡድኑ በሦስተኝነት የያዘው ጉዳይ መሆኑን ለቡድኑ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ነግረውናል።

LEAVE A REPLY