ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– አንድ ሳምንት በዘለቀው የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሦስትዮሽ ድርድር የተጠበቀውን ውጤት ማምጣት እንዳልቻለ ታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ሰሞኑን ሲካሄድ የቆየውን የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ግብጽ ከዚህ በፊት በድርድሩ ስታሳየው የነበረውን ሙሉ የዓባይ ውኃ ይገባኛል አካሄድ አሁንም እየተከተለች መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመናት የተከተሉት ይህ አካሄድ ለአሁኑ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን በምንም መልኩ የማያስኬድ ከመሆኑ ባሻገር ኢትዮጵያ በምንም መንገድ የማትቀበለው ሐሳብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አርብ ዕለት ተካሂዶ በነበረው ድርድር ላይ ግትር አቋም ይዛ የቀረበችው ግብፅ ድርድሩ ከሰኞ በኋላ እንዲቆም፣ ከዛ የሚረዝም ከሆነ ለማቋረጥ እንደምትገደድ መግለጿን ኢትዮጵያ ነገ መዘገቡ ይታወሳል።
ግብጽ አሁንም ፍላጎቷ ድርድሩ እንዲቋረጥ መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ ” ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ 2015 ከነበረው የመርህ ስምምነት ውጭ ሌላ መተሳሰሪያ የሌለን በመሆኑ ግብጽ ድርድሩን አቋርጣ የምትወጣ ከሆነ፣ ከዚህ በኋላ ለድርድር የምንቀመጥበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም” ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም ይፋ አድርገዋል።
“እየተደራደርን ያለነው ሁሌም እኔ ብቻ ልጠቀም ከምትለው፣ እድሜ ልኳን የኢትዮጵያን ጥቅም ከምትጻረረው፣ ሀገራችን ዘላቂ ጥንካሬ እንዳይኖራት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከምትሠራው ግብጽ ጋር ነው” በማለት የተናገሩት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የግብጽ ሕዝብ መንግሥታቸው ምክንያታዊና ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ ተመስርቶ እንዲደራደር ጫና ሊያሳድር ይገባል ብለዋል።