ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኦነግ የቀድሞ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ዲማ ነገዎ አሁን ሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር የፖለቲካ ልዮነት ቢኖራቸውም በሀገራዊ ጥቅም ላይ የጋራ መግባባትን እንደሚከተሉ ገለፁ።
በኦሮሞ የሕዝብ ትግል ውስጥ በዘመናት ውስጥ ከፍተኛ ትግል አድርጓል በሚባልለት ኦነግ ውስጥ የከረሙት ዲማ ነገዎ ፤ “የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖረንም በሀገራዊ ጥቅም እና ሉአላዊነት ላይ ግን የውስጥ አንድነትን ማጠናከር እና አንድ መሆን አለብን ” ሲሉ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ምሁር ናቸው የሚባልላቸው ዲማ ነገዎ ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ቀደም ባሉት ዘመናት ሱዳን እና ግብፅ ኢትዮጵያን ሳያማክሩ በአባይ ውኃ ላይ የተለያዩ ግድቦችን መሥራታቸውንም ያስታወሱት ዶ/ር ዲማ ነገዎ፤ ከዚህ አኳያ ሀገራቱ ኢትዮጵያም በራሷ ውኃ የመጠቀም መብቷን ሊገድቡ አይችሉም ብለዋል።
ግብፅ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያን ለመጉዳት እና ኢትዮጵያ እንድትዳከም ሥትሠራ እንደቆየችና አሁንም በውስጥ ጉዳይ በመግባት ልዩነት ለመፍጠር እየባዘነች መሆኑን አንጋፋው ፖለቲከኛ ገልፀዋል።