ህወሓት የድብቅ ድርድርና ውይይት እንደማይፈልግ ዶ/ር ደብረፂዮን ለሀገር ሽማግሌዎቹ ገለፁ

ህወሓት የድብቅ ድርድርና ውይይት እንደማይፈልግ ዶ/ር ደብረፂዮን ለሀገር ሽማግሌዎቹ ገለፁ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የህወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፂዮን ከህወሓት ጋር በድብቅ የሚደረግ ውይይትን አንቀበልም አሉ።

ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት አገራዊ መድረክ በማዘጋጀት ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ማድረግን እንጂ የድብቅ ድርድርን አንፈልግም ሲሉ ዶክተር ደብረፂዮን የተናገሩት፤ በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መስተዳደር መካከል ላለው አለመግባባት መፍትኄ ለማበጀት ዛሬ ወደ መቀለ ከተጓዙት የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ሲያደርጉ መሆኑ ታውቋል።
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች መማክርት፣ ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ፤ ሁለቱ ወገኖች ተቀራርበው በመነጋገር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በአስቸኳይ ግንኙነት እንዲጀምሩ ማሳሰባቸው ተነግሯል።
የህወሓት ሊቀ መንበርና የትግራይ ክልል መንግሥት ምክትል ርዕስ መስተዳድር  ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ውይይቱ የተናጠል ሳይሆን ሁሉንም አካላት ማካተት እንዳለበት መግለጻቸውን የዘገበው የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ፤  በዉይይቱ ላይ ፕሬዝዳንቱ “የውውይት መድረክ መፈጠር ካለበት፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች፣ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ፌደራሊስት ኃይሎች የሚሳተፉበት አገራዊ መድረክ መዘጋጀት አለበት እንጂ ከህወሓት/ትግራይ መንግሥት ጋር በድብቅ የሚደረግ ውይይት አንቀበልም፤ ትርጉምም አያመጣም” ብለዋል ሲል ይፋ አድርጓል።
 “ውይይቱ በመጨረሻ ሰዐት የተጀመረ ቢሆንም መሞከሩ ግን ጥሩ ነው” ያሉት አወዛጋቢው የህወሓት ሊቀ መንበር፤ “የአገሪቱን ችግር ለመፍታት የሚንቀሳቀስ አካል ችግሩ የተፈጠረው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ በአገሪቱ አምባገናናዊ ሥርዓት ለመገንባት እየተሯሯጠ በሚገኘው ብልፅግና የተሰኘው ቡድንና የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እንጂ በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል ብቻ የተፈጠረ አለመግባባት አድርጎ መመልከት አይገባም” ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶቹና የአገር ሽማግሌዎች ስለጦርነት አላስፈላጊነት መስበካቸው፣ ስለ ሰላምና ውይይት መናገራቸው ልክ መሆኑን ያመለከቱት ደብረፂዮን ” ነገር ግን ይህ መባል ያለበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማክበር ምርጫ አድርጋለሁ ባለው ክልል ላይ የጦር አዋጅ ለሚያውጀው የፌደራል መንግሥት ነው” ሲሉ የትግራይ ክልልና የህወሓት አካሄድ ትክክል መሆኑን ለማሳየት ሞክረዋል።

LEAVE A REPLY