ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ በተደረገው የ5 ሺኅ 274 የላቦራቶሪ ምርመራ ፤ አንድ መቶ ሀያ ዘጠኝ (129) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና ይህን ተከትሎ አጠቃላይ በሀገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3 ሺኅ 759 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው 79 ወንድና 50 ሴት ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ፣ የዕድሜ ክልላቸው ከ1 ዓመት እስከ 70 ዓመት እንደሆነ ያመላከተው መግለጫ፤ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች 85 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 5 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣ 11 ሰዎች ከአፋር ክልል፣ 11 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣ 10 ሰዎች ከሶማሌ ክልል፣ 7 ሰዎች ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ 6 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 1 ሰው ከአፋር ክልል እንዲሁም 4 ሰዎች ከድሬዳዋ መሆናቸውንም አረጋግጧል።
በሌላ በኩል በዛሬው ዕለት በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የ2 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ በሕክምና ማዕከል ውስጥ ሕክምና ሲደረግላቸው የነበሩ መሆናቸው ተሰምቷል። በዚህ መሠረት አጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ሥድሣ ሦሥት (63) ደርሷል፡፡
በተያያዘ መረጃ በትላንትናው ዕለት አንድ መቶ ዐሥራ አንድ (111) ሰዎች፣ (109 ከአዲስ አበባ እና 2 ከድሬዳዋ) ማገገማቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 849 ደርሷል።
2 ሺኅ 845 ሰዎች በአሁኑ ሰዐት በቫይረሱ ተይዘው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፣ 30 ሰዎች በፀና ታመው ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር መግለጫ ያሳያል።