ነገ የሚጀመረው የደቡብ ክልል ም/ቤት ጉባዔ በኤጄቶ ሊበጠበጥ ይችላል በሚል ሀዋሳ ከተማ...

ነገ የሚጀመረው የደቡብ ክልል ም/ቤት ጉባዔ በኤጄቶ ሊበጠበጥ ይችላል በሚል ሀዋሳ ከተማ በጸጥታ ኃይሎች እየተጠበቀች ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የተለያዮ ወሳኝና አከራካሪ ጉዳዮች ይስተናገዱበታል ተብሎ የሚጠበቀው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ ምክር ቤት  ጉባዔ ነገ ይጀመራል ተባለ።

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባዔውን ነገ በሐዋሳ ከተማ መጀመሩን ተከትሎ ከተማዋ ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገላት መሆኑን ታማኝ የዜና ምንጮቻችን ለኢትዮጵያ ነገ ገልፀዋል።
የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ዓለሚቱ አበበ የምክር ቤቱ ጉባዔ ከሰኔ 11/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ቀናት እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ የጉባዔው አጀንዳ ነገ የምክር ቤቱ አባላት በተገኙበት ይፋ እንደሚደረግ ዳይሬክተሯም አስታውቀዋል።
የነገው የደቡብ ክልል መንግሥት ምክር ቤት ስብሰባ  በሀዋሳ ከተማ ሲካሄድ በቅርቡ የክልልነት መብቷን በሕዝበ ውሳኔ ካረጋገጠችው ሲዳማ ክልል ጋር በተያያዘ በምክር ቤቱ አባላት (በተለይም በሲዳማ ተወላጆች) መሀል ከፍተኛ ውዝግብ ሊነሳ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
እንደ ታማኝ ምንጮቻችን ዘገባ ከሆነ ጉባዔው የሚካሄድባት ሀዋሳ ከተማ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ በልዮ ኃይል  ፖሊስ አባላትና በመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ ትገኛለች።
በተለይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የቀረበለትን የክልሎች 2013 ዓ.ም በጀት ሲያፀድቅ በበጀቱ ውስጥ ሲዳማን አለማካተቱ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞን አስነስቷል።
ይህን ተከትሎ ራሱን የሲዳማ ሕዝብ ተሟጋችና ነፃ አውጪ አድርጎ የሚያስበው ኤጄቶ የተሰኘው ቡድን፤ ነገ በሀዋሳ የሚካሄደውን ስብሰባ ሊበጠብጥ ይችላል የሚል ግምት በመኖሩ በክልሉና በፌደራል መንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥበቃ እንዲደረግ መወሰኑን የደረሰን መረጃ ያሳያል።

LEAVE A REPLY