ኢትዮጵያን እና ህዝቧን በተለያዩ አለማቀፍ የስፓርት መድረኮች ላይ ያስጠራው እውቁ እና አንጋፋው ቦክስኛው ሰይፉ መኮንን (ጢቦ) በአሜሪካው ፣ካሊፎርኒያ ግዛት ፣ሎሳንጀለስ ከተማ ውስጥ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።
እኤአ በ1953 በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አሌልቱ ውስጥ የተወለደው ሰይፉ እና አትሌቲክስ የተዋወቁት ገና የአስራ ሁለት አመት ጨቅላ ሳለ የአካል ማጎልበት እንቅስቃሴ በማዘወተሩ ሲሆን በሁዋላም እኤአ 1971 በታዋቂው ጥቁር አሜሪካዊው ቡጢኛ ፣መሀመድ አሊ ጥበብ እና ጀግንነት መማረኩን የተመለከቱት አሜሪካዊው አሰልጣኝ ኤድዋርድ ስምኦን በስልጠናቸው ውስጥ በማካተት ወደ ፕሮፊሽናል ቦክሰኛነት እንዲሸጋገር አድርገውታል።
እኤአ 1972 በጀርመን በተካሄደው የሙኒክ ኦሎምፒክ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ የቦክስ ቡድንን ወክሎ የተሳተፈው አትሌት ሰይፉ መኮንን በወቅቱ በኖሮዌዩ ሃራልድ ስኮግ በነጥብ ብልጫ ቢሸነፍም ከአጠቃላይ ሃያ ሰምንት አትሌቶች ስምንተኛ ደረጃ ለመውጣት ችሏል። ያንን የታሪክ አጋጣሚውን ለማስታወስ ሲልም በቀኝ ክንዱ ላይ ለዘላለም የማይጠፋ አምስት ቀለበቶችን መነቀሱ ተዘግቦለታል።
እኤአ በ1976 በሞስኮ፣ሩሲያ ተካሄዶ በነበረው የቦክስ ውድድር እንዲሁም በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተፎካካሪዎችን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያዎችን እና የተለያዩ ማበረታቻዌችን ያገኘው፣ አትሌት ሰይፉ የብሄራዊ የቦክስ አሰልጣኝ ለመሆንም በቅቷል።
በተፎካካሪዎቹ ላይ በሚሰነዝራቸው ከባባድ የቡጢ ውርጅብኞች የተነሳ አብዛኞቹን በዝረራ በማንበርከኩ በደጋፊዎቹ ዘንድ “ጢቦ” የሚል ስያሜ ያገኘው አትሌት ሰይፉ በስፖርት አለም ላበረከታቸው በርካታ አስተዋጽኦቹ ከግርማዊነታቸው ከቀዳማዊ ኃ/ስላሴ፣ ከኬኒያው ጆሞ ኬኒያታ፣ ከታንዛኒያው ጁሊየስ ኔሬሪ፣ ከአጋንዳው ኢዲያሚን ዳዳ እና መሰል የአፍሪካ መሪዎች እጅ የተለያዩ ሽልማቶችን ተቀብሏል።
ከዛሬ አስር አመት በፊት ደርሶበት የነበረውን የጤና መታወክ እና በህክምና ወጪውን ለመሸፈን በሎሳንጀለስ ከተማ የተካሄደው የኢትዮጵያኖች ወገኖቹ እና አድናቂዎቹ የድጋፍ ጥረትን ለመዘገብ በስፍራው የተገኘው እንደ ታዋቂው የሎሳንጀለስ ታይምስ ጋዜጣ ዘገባ ኤአአ በ1980ቹ መጀመሪያ ወደ አሜሪካ የተስደደው ሰይፉ ጢቦ በተለያዩ ምክንያቶች ከእናት አገራቸው፣ ከኢትዮጵያ የተራራቁ ኢትዮጵያኖችን እና ትውልደ ኢትዮጵያኖችን እንዲሰባሰቡ በሚያደረጉ ተሳትፎዎች ውስጥ ቤተክርስቲያን እንዲቋቋም፣የስፖርት ማእከል በማቋቋም፣ የአየር ሰአት በመግዛት የስፖርት ነክ የራዲዮ ጣቢያ ፕሮግራም በማዘጋጀት ..ወዘተ ጉልህ አሻራ የጣለ፣ በቦክሱ አለም ብቻ ሳይሆን በስደት ዘመንም ኢትዮጵያን እና ልጆቿን ያልዘነጋ፣ ለበርካታዎች ጥሩ ምሳሌ ለመሆን የቻለ ትልቅ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ገልጾታል።
ጀግና ይሞታል እንጂ ፣ገድሉ አይሞትም አንደሚሉት በተወለደ በስድሳ ሰባት አመቱ ከዚህ አለም በ አካለ እረፍት የተለየው ታዋቂው ቦክሰኛ ሰይፉ ጢቦ ቅዳሜ ሰኔ/ጁን 20,2020 እኤአ በሎሳንጀለስ ድንግል ማሪያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቤተሰቦቹ ብቻ በሚታደሙት የጸሎት እና የፍትሀት ፕሮግራም ይካሄድለታል። በተመሳሳይ ቀን የቀብር ስነ ስርዓቱ 6000 Blvd Santa Monica በሚገኘው Holly Wood For Ever የመካነ መቃብር ስፍራ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል ።