ኪሎ ሽንኩርት 35 ብር  የሸጡ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

ኪሎ ሽንኩርት 35 ብር  የሸጡ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ 35 ብር እንዲገባና ሌሎች የእህል ዓይነቶች ላይም ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዲፈጠር አድርገዋል የተባሉ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ።

ንግድ ሚኒስቴር የሽንኩርት ዋጋ መናር ምክንያት ላይ ጥናት በማድረግ ምክንያት ሆነው በተገኙ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ነው ሲልም ገልጿል።
 በሚኒስቴሩ የሚመራው የገበያ ማረጋጋት ብሔራዊ ግብረ ኃይል የሽንኩርት ዋጋ ጭማሪውን አስመልክቶ ጥናት አካሂዷል ያሉት ሚኒስቴር ዲኤታው አቶ እሸቴ አስፋው፤
በጥናቱ መሠረት ለሽንኩርት ዋጋ ጭማሪው የምርት እጥረት መኖሩ አንድ ምክንያት ቢሆንም፣ ችግሩ በዋናነት የተፈጠረው ግን የሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ተረጋግጧል ሲሉ ገልፀዋል።
ይህን ተከትሎ ሽንኩርትና ቲማቲም የመሳሰሉ አትክልቶች የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ሳያሟሉ ወደ ውጭ እንዳይወጡ፣ ለሁሉም የጉምሩክ ጣቢያዎች ደብዳቤ በመጻፍ ክትትል እየተደረገ እንደሆነም ታውቋል።
እስካሁን በተደረገው ክትትል ምርቶቹ በሱማሌ ክልልና በድሬዳዋ በማቆራረጥ ወደ ጂቡቲ፣ ሱማሊያና ኬንያ እየተላኩ መሆኑ እንደተደረሰበት የጠቆሙት ሓላፊ፤ ሕገወጥ ነጋዴዎች 11 መኪና ሽንኩርት ወደ ጅቡቲ ሲያስወጡ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አዳማ ላይ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና መሰል ምርቶችን በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ የተያዙ ስለመኖራቸውም ተሰምቷል።  ቀደም ሲል በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የሽንኩርት ምርት ከኮሮና መከሰት ጋር ተያይዞ መቅረቱ የራሱ ተፅዕኖ እንደነበረውም ተነግሯል።
በሱዳን በኩል የነበረው የሽንኩርት አቅርቦት የሚቀጥልበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን የገለፁት ሚኒስቴር ዲኤታው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አቅርቦትና ምርት ላይ የሚሠራው እንዳለ ሆኖ የኅብረተሰቡም ትብብር በመኖሩ ሕገወጥ ደላሎችና ነጋዴዎች ላይ የተጠናከረ እርምጃ ይወሰዳል መባሉንም ለማወቅ ተችሏል።

LEAVE A REPLY