ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ በተደረገው 4 ሺኅ 809 የላብራቶሪ ምርመራ አንድ መቶ ዐሥራ ሥድሥት (116) ሰዎች የኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 4 ሺኅ 070 መድረሱ ታውቋል።
ከተደረገው ጠቅላላ የላብራቶሪ ምርምራ ውስጥ 37 (24 ከጤና ተቋም እና 13 ከማኅበረሰብ በተወሰደ ናሙና) ናሙናዎች በአስክሬን ላይ የተደረገ የላብራቶሪ ምርምራ ሲሆን፤ አንድ ናሙና ከጤና ተቋም እና አንድ ናሙና ከማኅበረሰብ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አምስት በሕክምና ማዕከል ውስጥ በሕክምና ላይ የነበሩ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰምቷል። ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው እና ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ሠባ ሁለት (72) ደርሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዘጠና ሦሥት (93) ሰዎች (88 ከአዲስ አበባ፣ 2 ከአማራ ክልል፣ 2 ከሶማሌ ክልል እና 1 ሰው ከኦሮሚያ ክልል) ማገገማቸውን ተከትሎ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 1 ሺኅ 27 መድረሱ ተነግሯል።