የአየር ጠባይ – የሰሞኑ ንፋስ ከባድ ነበር፡፡ በተለይ ኅዳር 25 እና 26 ሁለቱን ቀናት አዲስ አበባ ብቻ ሣትሆን ብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በኃይለኛ የንፋስ ወጀብ ሲናጡ እንደነበር ከአንዳንድ አካባቢ በተገኙ የሥልክ ልውውጥ መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ብዙ ደካማ ቤቶች የቆርቆሮ ክዳናቸውን ተነጥቀዋል፤ የወያኔዎች ዜጎችን ከመረጃ ውጪ የማድረግ ዕኩይ ባሕርይ ካስከተለው የዲሾች መነቃቀል ባልተናነሰ ብዙ ዲሾች ተነቃቅለውና አቅጣጫቸውን ስተው ጥቂት የማይባሉ ምሥኪን ዜጎችን ላልታሰበ ወጭ ተዳርገዋል፤ የመብራትና የሥልክ ምሰሦዎች ወድቀው ከኃይል መቋረጥ በተጨማሪ ቀላል የማይባል ጉዳት አድርሰዋል፤ ዛፎች ከሥራቸው ተነቃቅለዋል፡፡ … ንፋሱ በዚህ ብዙም ባልተለመደና ባልተጠበቀም የማፍረስ ተግባሩ ሣይወሰን በተጓዳኝ ባስከተለው የጧትና የማታ ቅዝቃዜው በተለይ ባለጠጋዎችን ብዙ ጆንያ ከሰል እንዲጨርሱ አድርጓቸዋል፡፡ … ሁሉም ነገር ለበጎ ነው ብለን ዝም አልን – ለነገሩ ሌላ ምርጫም አልነበረንም፡፡
ይህ ሰሞነኛ የአየር ሁኔታ በባለሦስተኛ ዐይኖች የተለዬ አንድምታዊ ትርጉም ተሰጥቶት እንደነበር ለመደበቅ መሞከር ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም እኩለ ቀን ድረስ የነበረውን ሱሪና ቀሚስ አስወላቂ ወጀብ እንዲሁም በዚያው ሰሞን በተደረገ ሕዝባዊ የምህላ ቀን ሰማይ ላይ የደም አክሊል ባጠላበት ቀስተ ደመና ተከብባ የታየችውን ፀሐይ እንደመርሳት ይቆጠራል፡፡ እግዚአብሔር ይናገራል፡፡ የእግዚአብሔር ቋንቋ ሁሉም ነው፡፡ ግዑዛን ፍጥረታቱ ሳይቀሩ በግልጽ ይናገራሉ፡፡ ለርሱ የሚሣነው ነገር የለምና አሁንም እየተናገረ ነው፡፡ ሰሚ ግን የለም!
አቀባበል – ሰሞኑን በጣም የተደሰትኩበት ነገር አለ፡፡ በኢሳት እንደተከታተልኩት ግርማ መንገሻ የተባለ ወገናችን ጎራ ቀይሯል፡፡ ወደ ሕዝብ ተመልሷል፡፡ ወደ ሕዝብ ሲመለስም ከልባዊ ይቅርታ ጭምር መሆኑን በበኩሌ ተረድቻለሁ፡፡ በግድያና በእሥራት በቀጥታ ባይሳተፍም ከዚህ ቆሻሻ ሥርዓት ጋር በመቆየቱ ብቻ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከልቡ ይቅርታ መጠየቁን ስከታተል ዐይኖቼ ዕንባ አንቆርዝዘው በደስታ ስሜት ተዋጥኩ፡፡ በወያኔው አፍዝ አደንግዝ ተይዘው ነፍሳቸው ለምትቃትት ለሌሎች ወገኖቼም ይህን ዕድል ተመኘሁ፡፡ ይህ ግርማ መንገሻ የታደለ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈለጉን ይባርክልን፤ ሌሎችንም በሕዝባዊ ፍቅር ማርኮ ያምጣልን፡፡ ሙሤን ከፈርዖን ጎራ በጥበቡ ለይቶ ወደ ዘመዶቹ ያስገባና እሥራኤላውያንን ነፃ ያወጣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እነግርማን አብዝቶ የነፃነታችንን ቀን ያቅርብልን፡፡ አሜን፡፡
በሩ ሳይዘጋ፣ ይህ ወርቃማ ራስን የመፈተሸ ጊዜ ሳያልቅ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከወያኔ ጋር ሆነው ሕዝብንና ሀገርን እየበደሉ፣ ወንድምና እህቶቻውን እያሰቃዩና እየገደሉ የሚገኙ ወገኖቻችን በአፋጣኝ ወደ ኅሊናቸው ተመልሰው የሕዝብን የነፃነት ትግል እንዲቀላቀሉ እነሱንም ፈጣሪንም እንለምን፡፡
እዚህ ላይ ግን መረዳት ያለብን አንድ ትልቅ ነገር አለ – ይህ ከግርማ ጋር በፍጹም የማይያያዝ የእግረ መንገድ ማስታወሻ ነው፡፡ ይህም እውነተኛ ንስሃ ከ“ሲሞቅ በማንኪያ፣ ሲቀዘቅዝ በእጅ”” የተለዬ መሆኑን ነው፡፡ አንዳንድ አሰለጦች የአየሩን ጠባይ እያዩ ከአንጀት ሳይሆን ከአንገት በሚነሣ እስስታዊ አክሮባት ሕዝብን ለማታለል እንዳይሞክሩ እነሱም “እኛ” የምንባለውም መጠንቀቅ አለብን፡፡ በዚህን መሰሉ ወሳኝ ወቅት ይህ ዓይነቱ አደጋ መከሰቱ የማይቀር ነው – መልካችን፣ ቋንቋችን፣ ነገረ ሥራችን ባጠቃላይ … ተመሳሳይ በመሆኑና ሰው እንደስኳር ወይ እንደጨው ተቀምሶ ጤናማው ከበሽተኛው የሚለይ ባለመሆኑ ታጥቦ ጭቃ ከሚያደርጉን የገዛ ወገኖቻችን ራሳችንን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ ይበልጥ መጠንቀቅ ያለበት ደግሞ በወያኔዎችና አሰማሪዎቻቸው ብዙ ግፍና በደል እየደረሰበት ያለው የለውጡ ኃይልና ሁሉም ጭቁን ዜጋ ነው፡፡ ጎራ የሚለውጡ ሰዎችን እውነተኛ ፍላጎትና ተልእኮ ማወቅ ይቅርታ ይደረግልኝና እንኳንስ ለሰው ለፈጣሪም ሣይቀር የሚከብድ ይመስለኛል – ክርስቶስን ለስቅላት ያበቀው ይሁዳ እኮ ሰው ነበር፡፡ የዓዞ ዕንባ እያነቡ የሕዝብን የነፃነት ትግል በነቀርሣ ደዌ ከሚበክሉ ሆዳሞችና አጋሰሶች መጠንቀቅ ከዋናው ትግል የበለጠ ትኩረትና ጥንቃቄን ይሻል፡፡
ኅሊና የሌላቸው ዜጎች የሚያስከትሉት አደጋ ከባድ ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ በአመራርና በወሳኝ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚቀመጡ ከሆነ ትግላችን ሁሉ – እንደ እስከዛሬው – አድሮ ቃሪያ ከመሆን አይድንም፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ተሰቃይተናልና ከአሁን በኋላ ልብ መግዛት ይገባናል፡፡ አንዲት ግራም ጨው አንድ ጋን ሙሉ ጠላ እንደምታሾመጥር ካልገባን በምንሠራው ትንሽ ስህተት ዕድሜ ልካችንን ስናልቅስ እንኖራለን፡፡ ስለዚህ በተመላሽ ሰዎች ላይ የሚኖረን አመኔታ ገደብ ይኑረው፡፡ አንዳንድ ሰዎች አቋም የሌላቸውና የቀኑን ንፋስ ብቻ እየተከተሉ እንደገበታ ውኃ የሚዋልሉ፣ ያዋጣናል ወደሚሉት አቅጣጫም የሚነፍሱ መሆናቸውን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም፤ በይሉኝታና “ለትግሉ ስኬት ሊጠቅሙን ይችላሉ” ከሚል የዋህ ግን ጎጂ አስተሳሰብ ተነስተን ሁሉንም እያስጠጋን ጓዳችንን ብናሳይ የምንጎዳው እኛው ነን፡፡ ይህን ስል እንደግርማ ያሉ ቀደም ሲል ጀምሮም አስተዋፅዖ ያደርጉ የነበሩ ወገኖችን ባልተገባ ፈተና እናስጨንቃቸው ማለቴ አይደለም፡፡ የሚያብለጨልጭ ሁሉ ወርቅ አለመሆኑን እንወቅ እያልኩ ነው፡፡
ግዝትና ውግዘት፡ – ካህን ያልሆንኩ ጨዋ ሰው ነኝ፤ ማዕረገ ክህነት የሌለው ደግሞ መገዘት አይችልም፡፡ ማውገዝ ግን ይችላል፡፡ ለአሁን ግን ቄስ ልሁንና ልገዝት፤ ላውግዝም፡፡ ይገረም ዓለሙ የተባለ ጸሐፊ በዚህ ሰሞን በጻፈው አንድ መጣጥፉ አንተነህ ሙሉጌታ ስለተባለ አንድ አጋሰስ ያጋለጠው ነገር አለ – ሌላም ሰው ዛሬ ጧት ደግሞ ጽፏል – (ዛሬ የምለው 01/04/2009ዓ.ምን ነው)፡፡ ይህ ሰው የሆነውና ያደረገው ሁሉ እንደተባለው እውነት ከሆነ የኢትዮጵያ አምላክ ፍርዱን ይስጠው፤ ነፍሱም አትማር፡፡ መጪዋ ኢትዮጵያ ዕጣ ክፍሉ አትሁን፡፡ ብዙ ጥፋት ሳያደርስ ፈጣሪ አንድ ይበልልን፡፡ በክፉዎች ምክንያት ሀገርም ሕዝብም እንዳይኖረን ተደርገናልና እግዚአብሔር ክፉዎችን እንዲቀጣ መመኘትና መጸለይ ያን ያህል መጥፎ አይመስለኝም፡፡ የዚህን ምሥኪን ሕዝብ አበሳ የሚያበዛ ዋጋውን ያግኝ፡፡
ነፍስ ይማር – በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከወያኔው ሰው በላ ሥርዓት ጋር እየተፋለሙና ለሀገራቸው ነፃነት ውድ ሕይወታቸውን እየሰው ያሉ ወገኖቻችን አሉ፡፡ በአሁኒቷ ቅጽበት ራሱ ጠላትን ጥለው እነሱም እየወደቁ ነው፡፡ በዚያን ሰሞን ብዙ ግዳይ የጣለ ጀግና ተሰውቷል፡፡ እሱም ብቻ ሣይሆን ሌሎችም ተሰውተዋል፡፡ ነፃነት ቀላል አይደለችም፡፡ በልመናና በችሮታም አትገኝም፡፡ ወያኔዎች ይህን ቆሻሻ ዓላማቸውን ይዘው እንኳን በ17 ዓመታት ውስጥ የስንትና ስንት ሺህ ሰው ነፍስ ገብረው ነው አራት ኪሎን የተቆጣጠሩት፡፡ ስለዚህ መስዋዕትነቱ ገና ጀመረ እንጂ መገባደድ እንኳን አልያዘም፡፡ የትግል ጉዞው ብዙ መስዋዕትነትን እንደሚጠይቅና አልጋ በአልጋ እንደማይሆን መረዳት ይገባል፡፡ ዝንታለሙን እያለቀሱ ከመኖር ደግሞ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ከፍሎ ትውልድንና ሀገርን ማዳን የታላቅ ታሪክ ባለቤት ያደርጋልና ለነፃነት መሞት በተራ ጉንፋንና በእንቅፋት ከመሞት በተለዬ በእጅጉ ያኮራል፡፡ ለማንኛውም የነፃነት ታጋይ ሰማዕታትን ፈጣሪ ነፍሳቸውን ወደገነት ያስገባልን፡፡
አክራሪነትን እንዋጋ – የኢትዮጵያ ነፃነት ሸቀጥ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከየትም ሥፍራ በባቡር ወይ በመርከብና በአየር እንደሰው ተሣፍሮ ወይም እንደዕቃ ተጭኖ አይመጣም፡፡ ነፃነታችን ያለው እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ታግለን የምናገኘው እኛው ራሳችን ነን፡፡ በመሆኑም ከውጪ በሺዎች ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ተቀምጠን የምንማዘዘው ጦር ከንቱ ነውና አሁኑኑ እናቁመው፡፡ እርስ በርሳችን የምናደርገው ገመድ ጉተታ ኃይላችንን ያባክናል፤ ለጋራ ጠላታችንም ያመቻል፡፡ የግል ቂም በቀል ቢኖር ለትልቁ ሀገራዊ የነፃነት ትግል ሲባል መተው አለብን፡፡ በመለስተኛ ቅራኔዎች ትልቁ ሀገራዊ ጉዳይ መደብዘዝና የግፍና በደል አገዛዝ መቀጠል የለበትም፡፡ እስኪ አሁን እንኳን ነፍስ እንወቅ፤ ልብ እንግዛ፡፡ ወንድምና እህቶቻችን በረሃ ገብተው ድንጋይ ተንተርሰው ከጠላት ጋር በጥይት እየተተጋተጉ እኛ ምቹ ቦታ ቁጭ ብለን የነሱን መስዋዕትነት ዜሮ በሚያደርግ ውዝግብና እንካስላንትያ ውስጥ ስንገባ የነዚህ ውዶቻችን ደም ምን ይለናል? በርግጥም ቀኑ ሲደርስ ይፋረደናል!
ይሄ አማራ ኦሮሞ የምንለው የዘረኝነት አባዜ ደግሞ ዛሬውኑ ሊቀር ይገባዋል፡፡ በየጫካውና በየበረሃው ዜጎቻችን ከወያኔ ጋር እያደረጉት ያለው ፍልሚያ አንዱን ዘር በሌላው ለመተካት ሣይሆን ለሁላችን እኩል የምትሆን ሀገር ለመፍጠር ነው፡፡ ከ80 በላይ የሚገመቱ ጎሣና ነገዶች ባሉባት ሀገር ይህ አሁን የያዝነው የዘረኝነት ቅኝት አዋጭ እንዳልሆነ ከወያኔዎች ካልተማርን ከሌላ ከማንም አንማርም፡፡ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ይህን ማስተባበል አይቻልም፤ ሌላ አማራጭም ቢፈለግ አይገኝም፡፡ ስለሆነም ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነውና በርቀት የምትጯጯሁ ሰዎች አደብ ብትገዙ ይመረጣል፡፡ ሚዲያ መሥርታችሁ ሕዝብን ለመከፋፈል ሌት ከቀን የምትራወጡ ወገኖችም ብታርፉ ይሻላችኋል፡፡ ሕዝቡ አንቅሮ ሲተፋችሁ ያኔ ከምታፍሩ አሁኑኑ ልጓም አብጁና ወደኅሊናችሁ በመመለስ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር ለመራመድ ሞክሩ፡፡ የሕዝብ የጋራ ዕሤቶችን ማጥፋትና ማውደም ቢቻል ኖሮ ጥንት እንደዮዲት ጉዲትና እንደግራኝ አህመድ፣ አሁን በቅርቡ ደግሞ እንደደርግና እንደወያኔ የዚህችን ሀገር ቅርስ በአንድ ወይ በሌላ መልክ ለማጥፋት የሞከረ እንዳለመኖሩ፣ በአሁኑ ወቅት አንድም ሰው የኢትዮጵያን የቀድሞ ባንዴራ ሊያውቃትና ሊያውለበልባትም ባልቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን በምኞት የሚሆን ነገር ስለሌለ ይሄውና ሁሉም ለተወሰነ ጊዜ ተውተርትሮ ደክሞ ነው የቀረው፡፡ አሁንም ቢሆን አዲስ ባንዴራ ለማስለመድ የምትለፉ፣ ከሚያኮራን አፍሪካዊ አጻጻፍ በተለዬ አዲስ የፊደል ታሪክ ለማስፋፋት የምትጥሩ ወገኖች እፈሩና ጥቂት ለዘብ በሉ፡፡ ችግራችን የባንዴራ ሣይሆን ተደጋግሞ እንደተገለጸው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ እኛን የሚያሳክከን ሆዳችንን ሆኖ ሳለ እናንተ የምታኩልን ግን ጭንቅላታችንን ወይ እግራችንን ነው – “ያልተገናኝቶ ጅብ ጦሙን አደረ፣ አህያ እዚህ ሞቶ” እንዲሉ፡፡ አውሮፓና አሜሪካ እየተንደላቀቀ የሚኖር ሰው ስለኛ እውነተኛ ችግር ሊያውቅ ካልፈለገ መሠረታዊ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ችግር አለበት ማለት ነውና ይህን አሁን እየሠራው የሚገኘውን ታሪካዊ ስህተት የሚያወራርድበት ዘመን ሲመጣ እንዳያዝን አሁን ብዙም ሳይረፍድ የወንድምነቴን መምከርና ማስጠንቀቅም እፈልጋለሁ – ሳይወራረድ የሚቀር ምንም ዓይነት ዕዳ እንደሌለ ደግሞ እንወቅ፡፡ እናም እባካችሁን በዘውግ የወረት ፍቅር ያበዳችሁና የሰከራችሁ ሰዎች አቅል ግዙ፡፡ እንዲህ የምለው ለኛ ብቻ ሣይሆን ለእናንተም ጭምር ነው፡፡ የጠላቶቻችን መረማመጃ መሣሪያ በመሆን የታሪክ ተወቃሽ አትሁኑ፡፡ ኢትዮጵያንና ዕሤቶቿን ለማጥፋት የምታደርጉት ሙከራ ሁሉ በቅርብ እንደሚከሽፍ ተረዱ፡፡ ከፍ ሲል እንደተገለጸው ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት በፍጹም አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንኳንስ በምኞትና በከንቱ ስብከት፣ ላለፉት 25 ዓመታት በወያኔዎችና አለቆቻው በተግባርም ተሞክሮ እውን ሊሆን ያልቻለና ተስፋ ያስቆረጣቸው ህልምና ቅዠት ነው፡፡ ኮ/ል ደመቀንና ወ/ሮ ርስቴን ከወያኔዎች ጉያ፣ ኦባንግ ሜቶን ከጋምቤላ እምብርት፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑን ከጉራጌ ማሕፀን፣ ሡልጣን ሀንፍሬ አሊሚራን ከአፋር አብራክ፣ ሀሰን አብደላን ከሶማሌ … አውጥቶ ኢትዮጵያዊነት እንዲያንሠራራና እንዲለመልም እያደረገ ያለ መለኮታዊ ኃይል ከ14ሺ ኪሎ ሜትር በሚወነጨፍ የፕሮፓጋንዳ መርዝ ኢትዮጵያ ስትጠፋ ዝም ብሎ ያያል ማለት የዋህነት ነው፡፡ “ኢትዮጵያ ታበፅህ ዕደዊሃ ሃበ እግዚአብሔር” ተብሎ በመዝሙር በሚመለጠንበት ወቅት የዛሬዋ አሜሪካ ልትፈጠር ቀርቶ በማንም አእምሮ ውስጥ በሃሳብ ደረጃ እንኳን አልነበረችም፡፡
በጣም ከምወዳቸው መጽሐፍ ቅዱሣዊ ጥቅሶች አንደኛዋ ይህች ነች – ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፡፡ ለዛሬ አታስፈልገኝም እንጂ ሌላኛዋ ደግሞ ይህች ነች – እግዚአብሔር ክፉን ሕዝብ መቅጣት ሲፈልግ ጨካኝ ንጉሥ ይሾማል፡፡ ብዙ መንግሥታት በጊዜያቸው ኃይለኛና ጉልበተኛ ናቸው፡፡ ነገር ግን ለኩነኔም መጡ ለጽድቅ ዕድሜያቸውን ጨርሰው ሲሰናበቱ የነበራቸው ጥንካሬና ኃይል ሁሉ የእምቧይ ካብ ይሆንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ይንኮታኮታሉ፡፡ መሣሪያቸው፣ ወታደራቸው፣ ጋሻ ጃግሬያቸው፣ አጫፋሪዎቻቸው ሁሉ ይከዷቸውና ራቁታቸውን ይቀራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም ኃይለኛ ፍጡር የማይቀር የመጨረሻ ፅዋ ነው፡፡
የሩቆቹን የነሮምንና የነባይዛንታይንን ሥርወ መንግሥታት አነሳስና አወዳደቅ ሳንዘነጋ የነሂትለርንና የነሙሶሊንን ብርቱዎች መንግሥታት ብናስታውስ ታሪኩ ይሄው ነው፡፡ ባጭር ቃል – ተነሱ፣ ገነኑ፣ ወደቁ፡፡
አፄ ኃ/ሥላሤ እንደ አምላክ ያህል ይታዩ ነበር፡፡ እሳቸውን ያህል ገናና ንጉሥ በተራ ወታደርና በተራ የተማሪ ዐመፅ ይወድቃሉ ብሎ ያሰበ ቀርቶ ያለመ አልነበረም፡፡ ግን ጊዜ ደጉ ሁሉንም አሳየን፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አፍሪካን የሚያሰጋ የጦር ኃይል አደራጅቶ ሲያበቃ – እንዲያውም በፓርላማ ተብዬው ፊት “አንድ ሚሊዮን ተወርዋሪ ጦር አሰልጥነን ስናበቃ…” በሚልበት የመጨረሻ ሰዓቱ አካባቢ እዚህ ግቡ በማይባሉ ጭርንቁስ ተጋዳላዮች ሰበብ (ሰበብን አጥብቁልኝ!) ድምጥማጡ ጠፋ – ለምን ቢባል ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንማ! አምስት ተጋዳላዮች በተሠማሩበት የጦር ዐውድ በሺዎች የሚገመቱ ዘመናዊ ትጥቅ የያዙ ወታደሮች ለሀገር ሻጭ ወያኔ እጅ ይሰጡ ወይም እግር አውጪኛቸውን ይሸሹ ጀመር – ለምን ቢባል ሰዓቱ ደርሷላ! ልብ አድርጉልኝ – መቀሌ አካባቢ “ይሄው! አፈ ሙዙ ይሸተት! አልተኮስኩበትም…” ብሎ ለአንዲት ከበረት ደንብራ ላመለጠች ላም “እጁን የሰጠ” የደርግ ወታደር እንደነበር በጊዜው ሰምቻለሁ – ለምን ቢሉ ሰዓቱ በመድረሱ፡፡ ቀን ሲጎድል እንዲህ ነው፤ ወታደር ብትመለምል፣ በልዩ ኃይል ብታሰለጥን፣ ልዩ የጦር መሣሪያ ብትገዛ፣ ዓለም አቀፍ ቅጥር ነፍሰ ገዳዮችን በውድ ዋጋ ብታስመጣ፣ ዜጎችን ብታስር ብትፈታ … አይሆንም፡፡ ዕድሜ ሲደርስና ኃይለኛ ሲያረጅ እንደዚህ ነው፡፡ ቀን ከተቆረጠ ታንክና መትረየስ መጥፊያ እንጂ ማጥፊያ አይሆኑም፡፡ እንደለመድኩት አንዲት ፈገግ የምታሰኝ ነገር ጣል ላድርግ፡-
በቀ.ኃ.ሥ ዘመን ነው፡፡ ሽፍቶች አንድን አካባቢ ማጥቃት ያዙ አሉ፡፡ እነዚህን በጥባጭ ሽፍቶች ለመያዝ ወይ ለመግደል መንግሥት አንድ የመቶ ጦር ያሰማራል፡፡ ጦርነቱ አልቆ የመቶ መሪው ማታ ላይ ከጓደኛው ጋር በመሸታ ቤት እየተጨዋወተ ነው፡፡
እንዴት ነበር ጦርነቱ?
በስማም! ምኑ ይወራል በጣም ኃይለኛ ነበር!
እንዴ፣ ያን ያህል?
ያን ያህል ትላለህ? አለቅን እንጂ ምን ተረፍን!
በእናንተ በኩል ብዙ ሰው ሞተባችሁ?
አዎ፣ ብዙ አለቀብን፤ ለወሬ ነጋሪ የተረፍነው ከኔ ጋር በጣም ጥቂት ነን፡፡
እንዴ? የገጠሟችሁ ሽፍቶች ምን ያህል ቢሆኑ ነው?
አሃ፣ ብዙማ ቢሆኑ በምን ዕድላችን! አንድ ሽፍታ ገጥሞን ውር ውር እያለ ጨረሰን እንጂ! እዚህ ነው ስንለው እዚያ ነው፤ እዚያ ነው ስንለው ደግሞ እዚህ ነው፡፡ ፈጀን እንጂ አንተዬ!…
በጎጃምና በጎንደር “ውር ውር” እያሉ የወያኔን መንግሥት መቆሚያ መቀመጫ እያሳጡ ያሉ የነፃነት ኃይሎች በለስ የሚቀናቸው ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ እየበዙም እንደሚሄዱ ግልጽ ነው፡፡ አንድ የነፃነት ታጋይ ወይም ጥቂት አርበኞች ብቻ 50 እና 60 እንከፍ የወያኔ ጀሌ እየገደሉ እንደሚገኙ እንሰማለን፡፡ መቶና ሁለት መቶ ቆራጥ የነፃነት አርበኛ ስንትና ስንት ግዳይ ሊጥል እንደሚችል እንግዲህ ማሰብ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው የሰው ብዛትና የመሣሪያ ጥራት አይደለም – እርግጥ ነው ሁለቱም በጣም አስፈላጊ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ዋናው ግን ትንሽ ዕድል፣ ብዙ መለኮታዊ ባርኮትና የቆረጠ ልብ ነው – ለዚህ ደግሞ ቅን ዓላማና ሦምሦናዊ እምነት ያስፈልጋል – ከደግነትና ከይቅርባይነት ጋር፤ ክፋትንና በቀለኝነትን ከመጠየፍ እውነተኛ ጠባይ ጭምር፡፡ እምነት፣ ተስፋና ወኔ ከምንም በላይ ያስፈልጋሉ፡፡ የወገን ደጀን ደግሞ ከሁሉም በበለጠ ወሳኝ ነው፡፡ ይህ የነፃነት ትግል የሚደረገው የማይነጥፍ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚና የቁሣቁስ ድጋፍ ካለው የወያኔ መንግሥት ጋር መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ሌሎቻችንና ነፃነቱ የሚያስፈልገን ወገኖች የምንችለውን ሁሉ ካላደረግን ነፃነታችን በየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው የሚገኝ የዝክር ጠበል ጠዲቅ አይደለም፡፡ የሚመጣን ከመምጣት የሚያግደው እንደሌለ ባውቅም ይህን ትግል ከመርዳት እንዳንቦዝን የበኩሌን ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ኋላ ለኅሊና ፀፀት እንዳንዳረግ ደግሞ ቢያንስ አደናቃፊ ሆነን ላለመገኘት መጣር ይኖርብናል፡፡ አንድ ነገር ስናደርግ በትንሹ ሁለትና ሦስት ጊዜ ብናስብ ሀገርንም ራሳችንንም እንጠቅማለን፡፡ ጀርጃራ አንሁን፡፡ “አንዴ ከመቁረጥህ በፊት አሥሬ ለካ” አይደል ብሂሉስ? በዚያ ላይ ደግሞ ልጅና የልጅ ልጅ የሚባል የትውልድ ጣጣ መኖሩን አንርሳ፡፡ ምትኮቻችን አይፈሩብን፡፡
በነገራችን ላይ “የነፃነት ኃይሎች” የሚለው አጠራር በጣም ወድጀዋለሁ፡፡ ምናልባት አንድ ወቅት ወደ አንድ ነፃ ግዛት ሄጄ ሳለ ሕዝቡ በዚህ ስያሜ ሲጠቀም በመስማቴም ሊሆን ይችላል የወደድኩት፡፡ ስለሆነም ይህን ስም ሁላችንም ብንጠቀምበት እንደ አስተያየት ጠቆም ማድረግ እፈልጋለሁ – በዚህ አጋጣሚ፡፡ አሻሚም አይደለም፤ ከማንምና ከምንም ጋርም ተዳብሎ ይበልጥ አይወደድም ወይም አይጠላም፡፡ አማካይ ስያሜ በመሆኑ ውብ ነው፡፡ ደግሞም በስያሜዎች መጣላት ጊዜው ሊያልፍበት ይገባልና በከንቱ አንራኮት፤ እስኪ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንፋቀር ወንድሞቼ! የተጣላንም እንታረቅ፡፡ “ቂም ይዞ ጸሎት ሣል ይዞ ስርቆት” እንደሚባለው በሰበብ አስባብ እየተገፈታተርን ወደ አንድ የነፃነት ዒላማ መድረስ ይከብደናልና እባካችሁን የዘመናት ቂምና በቀል የቋጠርን ዜጎች ከዚህ መጥፎ ባህል እንውጣ፤ በስደትም ሆነ ሀገር ውስጥ ጎራ ለይተን መናቆራችን ከጠላቶቻችን ውጪ ለኛ እንዳልጠቀመን እስኪበቃን አየነው፡፡ የ“አሸናፊ”ና የ“አቸናፊ” ልጆች ሆነን በሆሄያት ልዩነት ሣይቀር የዚያና የዚህ ቡድን አባል እያልን እየተፈራረጅን መቆራቆሳችን ከአሁን በኋላ ያብቃ፡፡ በቃላት ስንጠቃ ልጆቿ የተገዳደሉባትና የሚገዳደሉባት ብቸኛ ሀገር የኛዋ ትመስለኛለችና እባካችሁን ከእህል ባለፈ ሆደ ሰፊነትን ገንዘባችን እናድርግ፡፡ ሁሉም እኮ ያልፋል!
ሟችና ገዳይን በሚመለከት አንድ ነገር ልበል፡፡ እኔ በመሠረቱ በማንም ሰው መሞት አልደሰትም፤ ምርጫ እያጣሁ ግን ከሁለት ሟቾች ለአንዱ ይበልጥ አዝናለሁ ወይ ባንደኛው ሞት ብዙም እዳላዝን እሆናለሁ – ይህም መረገም መሆኑን እረዳለሁ፡፡ እንጂ ሟችና ገዳይ የአንዲት እናት ልጆች በሆኑበት ሁኔታ አዘናችን ቅጥ አጥቶ የተቸገርን ዜጎች ጥቂት አይደለንም፡፡ እግዚአብሔር መፍትሔውን በአፋጣኝ ካልሰጠን ይህ ጅልነታችን ብዙ ነገር እያሳጣን ነው፡፡ለልማት የሚፈለግ የሰው ኃይልንና የደቀቀ ኢኮኖሚን አላግባብ እያባከንን እስከመቼ እንደምንገፋ አላውቅም፡፡ እነሱም ልባቸው ደነደነ፤ እኛም “ኃጢኣታችን በዝቶ” የፈጣሪ ምሕረት ራቀን፡፡ የሚገርሙ ጫፎች!
… ወያኔዎች ኃይላቸውን ጨርሰዋል፡፡ የቀራቸው ነገር ቢኖር በፊዚክስ inertia በመባል የሚታወቀው አንድ ነገር ባለበት የመቀጠል ክስተት ነው – የተሻለ ገፊ ኃይል እስኪያገኝ፡፡ ከወያኔዎች ቀጥሎ ያለው ሁኔታ ነው በጣም ሊያስጨንቀን የሚገባ – እንዲህም ስል “የምትስቅ ሴትና የሚነቃነቅ እንጨት” ያላቸውን ተግዳሮታዊ እልህ አስጨራሽነት እንዳልዘነጋሁ ይታወቅልኝ – አነጋገሬ እንደ አጠቃላይ እውነት እንዲወሰድልኝ እፈልጋለሁ፡፡ እንጂ ወያኔን በአንድ ጣት ገፍትሮ የመጣል ያህል ቀላል ነው ብዬ የማምን ሞኝ አይደለሁም፡፡ በሌላም በኩል ሁላችን ከገጠር እስከ ከተማ ብንተባበር በአንድ ጀምበር እንደጪስ በንነው ሊጠፉ የሚችሉ ቀላል ጠላት መሆናቸውን አምናለሁ፡፡ ጠላትን የምታከብደውም ሆነ የምታቀልለው አንተው ነህ፡፡ የጠላት ግዝፈት አንዳንዴ አእምሮ ውስጥ እንጂ በተግባር ባዶ ሊሆን ይችላል፡፡ ወያኔም ውስጡ ባዶ የሆነ ግን ሕዝብን በማስፈራራት በሥነ ልቦና ብቻ ግዝፈትን ያገኘ የዐረመኔ ወሮበሎች ጥርቅም ነው፡፡ ወያኔ ያሰቃያል – ስለዚህም ሕዝብ ይፈራዋል፡፡ ከዚያ ውጪ ምን አለው? ትልቁ የወያኔ ጦርና ሥልጣን ላይ የመቆያ ብልሃት በየእሥር ቤቶቹ ንጹሓን ዜጎች ላይ የሚፈጽመው የስቃይ ድርጊትና እንደመንግሥት አቋም ወስዶ የሚራምደው የብቀላ ሥርዓቱ ናቸው፡፡ ሌላ ተዓምር የለውም፡፡
በዚህ ከወያኔ በኋላ ስለሚጠብቀን አስጨናቂ ኃላፊነት ዙሪያ በተለይ ዲያስፖራው ምን ማድረግ እንዳለበት ብዙ መነጋገር ይኖርብናል፡፡ በበኩሌ የሀገራችን አንዱና ትልቁ ተስፋ ዲያስፖራው ነው ብዬ አምናለሁ፤ ምክንያቱም ከነሞራሉና ከነባህሉ ነው የተሰደደው ብዬ እገምታለሁና፡፡ በሀገር ውስጥ ከሞላ ጎደል ሁሉም ነገር ተበለሻሽቶ አይሆኑ ሆኗል፤ በአራቱም አቅጣጫ ሳማትር ሁሉም ነገር ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ ማይምነት ነግሦ፣ ሆድ አምላኪነት ገንኖ፣ ሃይማኖት ጠፍቶ፣ ኅሊና ወደ ሆድ ወርዶ ቦርጭ ውስጥ ተሸጉጦ፣ ቃልቻና ፓትርያርክ ሳይቀር ከጎጠኞቹ መንደር መሽገው ከዚያው ጎራ አመራር እየተቀበሉ በሚገኙበት ክፉ ዘመን፣ ቄስና ደብተራ ለሥጋው አድሮ የማይሠራው ወንጀል የሌለው መሆኑን እያየን ባለንበት ዕኩይ ወቅት፣ ሙስና የሀገር ባህልና የዕለት ተለት እስትንፋስ ሆና የትኛውም ቢሮ ሄደህ እጅህን ካልዘረጋህ አንድም ጉዳይ የማይፈጸምልህ ሀገራዊ ውርደትና ቅሌት በነገሠበት ዘመነ ደይን(መከራ)፣ የትምህርቱ ሥርዓት ተግማምቶ ስማቸውን እንኳን አስተካክለው መጻፍ የሚቸገሩ የፒኤችዲ ተመራቂዎችን እየታዘብን ባለንበት አጠቃላይ የክስረት ዘመን … ከኢትዮጵያ ብዙም ደግ ነገር ባንጠብቅ አይፈረድብንም፡፡ የሀገራችን ችግር ለወሬ እንኳን አይመችም፡፡ ለማንኛውም ሰላም፡፡
ንጉሥ በሠራዊቱ ታላቅነት አይድንም፤ጀግናም በኀይሉ ብርታት አያመልጥም። (መዝ. ዳዊት 33፡16)
No king is saved by the size of his army; no warrior escapes by his great strength. (Psalms 33:16)
/teshalem1@gmail.com/