ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ስምንት ዞኖች ላይ የአንበጣ መንጋ እየታየ መሆኑ ተነገረ።
የክልሉ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን እንደ ገለጸው ከሆነ የአንበጣ መንጋው በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ወደ አካባቢዎቹ እየገባ ነው።
በተለይም ባሌ እና ቦረና ባሉ ዞኖች ውስጥ መንጋው ከዚህ ቀደምም ሦስት እና አራት ጊዜ ተከስቶ ነበር።
የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገረመው ኦሊቃ ፤ የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች የአንበጣ መንጋውን በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ከወዲሁ መክረዋል።
የአንበጣው መንጋ እየጨመረ፣ ሁኔታውም እየከፋ የሚሄድ ከሆነ ግን በግብርና ሚኒስቴር አማካይነት በአውሮፕላን የመድኃኒት ርጭት እንደሚካሄድ ሓላፊው አስታውቀዋል።
ከአንበጣ መንጋው በተጨማሪ በምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ የክልሉ አካባቢዎች ጎርፍ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ የገለጹት አመራሩ፤ ጎርፉ ከተከሠተ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን ለኮሮና ቫይረስ ሳይጋለጡ ወደ የት አካባቢዎች መውሰድ ይቻላል የሚለው ላይ ከወዲሁ እየታሰበበት እንደሆነ አስረድተዋል።
የኦሮሚያ ክልል በአሁኑ ወቅት በመደበኛነት ድጋፍ የሚያደርግላቸው 2.4 ሚሊየን ዜጎች እንዳሉትና
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ደግሞ እስከ 2.2 ሚሊየን ተጨማሪ ሠዎች ድጋፍ ለመጠበቅ ይገደዱ ይሆናል የሚል የመጀመሪያ ዙር ጥናት እንደ ደረሰውም ለማወቅ ተችሏል።