በመቶዎች የሚቆጠሩ በቤይሩት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች  ጎዳና ላይ ወድቀዋል

በመቶዎች የሚቆጠሩ በቤይሩት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች  ጎዳና ላይ ወድቀዋል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በሊባኖስ እየተባባሰ የመጣውን የሊባኖስ ምጣኔ ሀብት ማሽቆልቆል ተከትሎ በርካታ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሊባኖሳውያን ጭምር ለቤት ሠራተኞቻችን መክፈል አንችልም በሚል ኢትዮጵያውያንን እያባረሩ ናቸው ተባለ።

ቁጥራቸው 100 የሚደርስ ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞችን በያዝነው ሳምንት በመዲናዋ ቤይሩት በሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ በር ላይ አሠሪዎቻቸው አምጥተው ጥለዋቸው ሄደዋል።
የቢቢሲው ጋዜጠኛ ማርቲን ፔሽየንስ ሦስት ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች በአንድ ሰዓት ውስጥ በቆንስላው በር ላይ አሠሪዎቻቸው አትተዋቸው ሲሄዱ መመልከቱን ዘግቧል።
በሁኔታው ክፉኛ የተደናገጡ በርካታ ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞች ሲብረከረኩ፣ ሲያለቅሱ እንዲሁም የሚሄዱበትና የሚጠለሉበት ጠፍቷቸው ሲጨነቁ፤ አንዳንዶቹም ግራ በመጋባት ሲንቀጠቀጡና ሲጮኹ መመልከቱን የጠቆመው ጋዜጠኛ አንድ አሠሪ ከኋላ ያነገተውን ሽጉጥ መዝዞ ጥሏት የሄደውን ኢትዮጵያዊት ሠራተኛ ሲያስፈራራ ተመልክቻለሁ ብሏል።
በኢትዮጵያ ቆንስላ በር፣ ቅዝቃዜው  በበረታው አስፓልት በስስ ምንጣፍ ላይ ተኝተው የሚያሳየውም ምስል በማኅበራዊ ሚዲያዎችና በተለያዮ ዓለም ዐቀፍ የዜና አውታሮች ከተለቀቀ በኋላ በርካቶች የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መንግሥት በአስቸኳይ ዜጎቹን ማውጣት አለበት እያሉ ነው።
የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝን ተከትሎ በደረሰው ጫና ምክንያት አሠሪዎቻቸው ደምወዝ ሳይከፍሉ ኢትዮጵያውያኑን ያባረሯቸው በመሆኑ ፤ በርካታ ሠራተኞች የሚላስ የሚቀመስ እንዳጡ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ጎዳና ከወደቁት የቤት ሠራተኞች መሀል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ ሎሚ የወራት ደምወዟ በአሠሪዋ ያልተከፈላት መሆኑን አስታውሳ፤ “ወደአገራችን እባካችሁ መልሱን፤ አሠሪዎቻችን ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ አላገኙንም ፤ እኛ ቆሻሻ አይደለንም እንደዚህ እንደ ቆሻሻ የሚወረውሩን” ስትል የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትን ተማጽናለች።
“በረራ እስኪጀመር ድረስ ቤትውስጥ እንዲቆዩና የሚሰሩበትም መንገድ እንዲመቻችላቸው፣ በቆንስላው ውስጥም ባሉ መጠለያዎች ውስጥ በጊዜያዊነት ማረፊያ እንዲሰጣቸው ጠይቃለች።

LEAVE A REPLY