“አባይ ለግብጽ፣ለኢትዮጵያ ምንእንደሆነ እናውቃለን” ሶማሊያ || (ታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)

“አባይ ለግብጽ፣ለኢትዮጵያ ምንእንደሆነ እናውቃለን” ሶማሊያ || (ታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)

በትላንትናው ፣ማክሰኞ እለት የአረብ ሊግ አባላት በኢትዮጵያው ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ በሰጠው ውሳኔ ላይ እንደ ጅቡቲ እና ኳታር ሁሉ ከግብጽ ጎን ያልቆመችው፣ ጎረቤት ሶማሊያ ኢትዮጵያም ግብጽም በጋራ ሊያድጉ እንደሚገባቸው አቋሟን ገለጸች።

የአባል አገራቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስተሮች በኢንተርኔት (ቨርቺዋል)አማካኝነት በወቅታዊው የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ውዝግብ እና በሊቢያ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ውይይት የታደሙት፣ የሶማሊያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስተር አምባሳደር አህመድ ኤሲ አወድ”የአባይ ውሃ ለግብጾች እና ለሱዳኖች የህይወት ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ፣ለ ወዳጃችን ለኢትዮጵያም የልማት ጉዳይ እንደሆነ እናውቃለን።ከዚህ አኳያ ሶስቱም አገራት ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ፣ውጥረቱን እንዲያለዝቡ ጥሪ እናቀርባለን”ብለዋል።

ቀደም ባለ ጊዜ ከግብጽ ጋር ጤናማ ግኑኝነት የሌላት፣ ኳታር “የህዳሴው ግድብን በገንዘብ ትረዳለች፣በወታደራዊ ኃይልም ኢትዮጵያን ታጠናክራለች “የሚል አሉባልታ ከወደ ካይሮ የተነዛባት ሲሆን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ዘገባውን ማስተባበላቸው ይታወሳል።

እንደ አረብ ሊጉ ሁሉ ሰኞ እለት በቃል አቀባዩ ስቲፋኒ ዱጁሪክ በኩል መግለጫ ያወጣው የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት (የተመድ) በበኩሉ ” የኢትዮጵያ፣የግብጽ እና የሱዳን መንግስታት ተቃርኖን አስወግዳችሁ በጋራ ለመስራት ሞክሩ” በማለት በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ አሳስቧል።

የአረቡ ሊግ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ከፍተኛ የቅስቀሳ ዘመቻ ያደረገችው ግብጽ የውጪ ጉ/ሚ/ሯ ሳሚ ሽኩሪይ ከአሜሪካው አቻቸው(ሴክሬታሪ ኦፍ ስቴት) ማይክ ፖምፔዬ ጋር ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች በተለይ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በስልክ መነጋገራቸውን እና ድርድሩ የተደናቀፈው “በኢትዮጵያ አሻፈረኝ ባይነት” እንደሆነ ሽኩሪይ ለፖምፔዎ ማስረዳታቸውን ከካይሮ መንግስት የውጪ ጉዳይ ሚኒስተር የወጣው መግለጫ ገልጿል። በህዳሴው ድርድር ላይ እራሱን ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት ያሸጋገረው የአሜሪካ አስተዳደር ቀደም ባሉት ጊዜያት ለግብጽ የወገነ የሚመስል መግለጫ ማውጣቱ አይዘነጋም።

 

LEAVE A REPLY