በሺኅዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ቤት ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ ላይ ናቸው ተባለ

በሺኅዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ቤት ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ ላይ ናቸው ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው (በሺኅ የሚቆጠሩ) ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሳኡዲ ዓረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው ተባለ።

ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ስደተኞች በጠባብ እና ሞቃታማ ቦታ ላይ በአንድ ላይ ታጭቀው በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ስደተኞቹ  ለቢቢሲ መላካቸው ታውቋል።
 ከሦስት ወራት  በፊት ከየመን ወደ ሳዑዲ ሊሻገር ሲል በሳዑዲ ፖሊስ ተይዞ አሁን ወዳለበት እስር ቤት መጣሉን የገለጸ አንድ ወጣት፤  “በሽንት ቤት ውስጥ ነው ያለነው፣ እዚያው እንበላለን፣ ከሽንት ቤት ውኃ እንጠጣለን። ውኃም በሦስት ቀን አንዴ ነው የሚመጣው። እየኖርንበት ያለው ቦታ ልንተኛበት ይቅርና ለማየትም የሚያስጠላ ነው። እላያችን ላይ ሰገራ እየፈሰሰብን ነው” ሲል ያለበትን ሁኔታ ጠቁሟል።
በተለያዩ አሰቃቂ እስር ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ ስደተኞች እስካሁን ሠባት ሰዎች እንደሞቱና አንዱ በሳዑዲ የፀጥታ አካላት  የተገደለ ነው ያለው ወጣት፤  ከመካከላቸው የሞቱ ሰዎች ቢኖሩም እስከ አሁን የሚረዳቸው ሰው እንዳላገኙም ይፋ አድርጓል።
 “በአንድ ቀን ሦስት ሰዎች ሞተውብን ዝም ብለው እንደ ቆሻሻ ተጥለዋል። አሁን ራሱ ሊሞት የደረሰ ሰው አለ፤ እኛን የሚረዳ ሰው ማን እንደሆነ አናውቅም፤ መፍትኄ አጥተናል። ይህንን የምትሰሙም እባካችሁ እርዱን። ከዚህ ሞት አውጡን” ሲልም ወጣቱ በቢቢሲ በኩል ለኢትዮጵያውያን ተማፅዕኖውን አሰምቷል።
በዚያው በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አስተባባሪ የሆኑት አቶ መሀሪ በላይ ትናንት ረፋድ ላይ ስደተኞቹን ለመጎብኘት ባቀኑበት ወቅት፤ ስደተኞቹ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ መመልከታቸውን አረጋግጠው፤ “በእስር ቤቱ ያለው ቆሻሻ፣ ረሃብና ሁሉም ችግር የታወቀ ነው፤ የታመሙት ሕክምና እንዲያገኙ እንዲሁም ወታደሮች ጉዳት እንዳያደርሱባቸው ተነጋግረን ተመልሰናል” ብለዋል።
“እነኚህ ዜጎች ከየመን ሲመጡ፤ ልብስ የላቸው፣ ጫማ የላቸው፣ አንድ ቲሸርት ብቻ ለብሰው ነው የመጡት። አንድ ቲሸርት ለብሰው ለሦስት ወራት ያህል በአንድ እስር ቤት ቁጭ ሲሉ፤ በዚያ ላይ አሁን ባለው ከፍተኛ ሙቀት ተጨናንቀው እየደረሰባቸው ያለውን ጉዳት መገመት አያዳግትም” ያሉት የኮሚኒቲው አስተባባሪ፤በእስር ቤት የሚገኙት ኢትዮጵያውያንን መንግሥት በፍጥነት የሚወጡበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።

LEAVE A REPLY