ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የፎቶግራፍ ምስሎችን በማንሳት ስመ ገናና ከሆኑት ምርጥ ካሜራዎች መካከል አንዱ የነበረው ኦሊምፐስ ካሜራ መመረት ቆሟል ተባለ።
ልክ እንደ ኒከን፣ ሶኒና ካነን ሁሉ በመላው ዓለም እውቅ ካሜራ ሆኖ ዘመናትን ነተሻገረው ኦሊምፐስ፤ በዓለም ግዙፍ ከሚባሉ ካሜራ አምራቾችም አንዱ የነበረ ቢሆንም፣ ካምፓኒው ከ84 ዓመታት በኋላ የካሜራ ምርቱን የሚመለከተውን ክፍል ለጃፓኑ ኢንዱስትሪያል ፓርትነርስ መሸጡን ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በዚህ ዘመን የካሜራ ቢዝነስ ምንም ሊያዋጣ አልቻለም የሚለው ዕድሜ ጠገቡ ካምፓኒ፤ ዘመናዊ ካሜራ የተገጠመላቸው ዘመናዊ ስልኮች ገበያውን ማጥለቅለቃቸው ለገበያው መዳከም ምክንያት እንደሆኑት ገልጿል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ምርት ላለማቆም በኪሳራ ሲንገታገት መቆየቱን ያስታወሰው ካሜራ አምራቹ፤ የመጀመሪያውን ኦሊመፐስ ካሜራ ምርቱን ለገበያ ያቀረበው በ1936 እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር እንደነበርና፤ ኩባንያው ከዚያ በኋላ ምርቱን እያሻሻለ አንድ ክፍለ ዘመን ሊያስቆጥር ጥቂት ዓመታት ሲቀሩት በቃኝ ብሎ የካሜራ ምርቱን ለሌላ ድርጅት ለማስተላለፍ ተገዷል።
በዓለም ላይ ተመራጭ የሆነው ኦለምፐስ ካሜራ በሰማኒያ አራት ዓመቱ ብዙ ጥሏል፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰርግ፣ ቀለበት፣ ልደት፣ ክርስትና መሰል የደስታ ጊዜ ትውስታቸውን በዚሁ ካሜራ ማስቀረት ችለዋል።
አፄ ኃይለ ሥላሤን ጨምሮ በርካታ የወቅቱ ሹማምንትና ልጆቸቸው በሀገር ውስጥም ሆነ በባህር ማዶ ቆይታቸው መንግሥታዊም ሆነ ግላዊ ጉብኝታቸውን በትውስታ ያስቀመጡት በዚሁ ካሜራ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዐሥራ ሠባት ዓመታት ኢትዮጵያን የመሩት የኮለኔል መንግሥቱ የፕሮቶኮል ክፍልና የደርግ የጽ/ቤት የካሜራ ባለሙያዎቻቸው በስፋት ይጠቀሙት የነበረው፣ የፕሬዝዳንቱን ጉብኝትና ስብሰባዎችም በዚህ ኦሊምፐስ በተሰኘው ካሜራ እንደሆነም ይነገራል።