አዲስ አበባ፤ ዳቦ፣ የመኖሪያ ቤት፣ መብራት እና ውሃ፣ የመሬት ቅርምት፣ ተረኝነተ፣ ሙስና፣...

አዲስ አበባ፤ ዳቦ፣ የመኖሪያ ቤት፣ መብራት እና ውሃ፣ የመሬት ቅርምት፣ ተረኝነተ፣ ሙስና፣ ግፍ፣ ወዘተ …

አዲስ አበባ ብዙ ሥር የሰደዱ እና ውስብስብ ችግሮችን በጉያዋ የያዘች ጉደኛ ከተማ ነች። ልክ እንደ ከተማዋም አዲስ አበቤዎችም እንዲሁ ከዳቦ አንስቶ እጅግ ብዙ እና ውስብስብ የመብት እና የጥቅም ጥያቄዎች እንዳረገዙ ከዚህ ሁሉ ጭንቅ የሚገላግላቸው አስተዳደር ሲናፍቁ ዘመናት ተቆጥረዋል። ይህ ችግር በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ምን ያህል ሊከፋ እንደሚችል መገመት ይቻላል።

የኋላውን ትተን ባለፋት ሁለት አመታት መስተዳድሩ እና የፌደራል መንግስቱ ከተማዋን ለማዘመን በሚል አዳዲስ እቅዶችን ይዘው እና አንዳንዱንም ጀምረው የከተሜውን ቀልብ ለመግዛት ጥረዋል። እነዚህ የተጀመሩ አንዳንድ የልማት እቅዶች በእርግጥም ከተማዋን ለማዘመን ይረዱ ይሆናል። ነገር ግን የከተማዋን ሕዝብ የቆዩ እና ውስብስብ ችግሮች የሚፈቱ ስለመሆናቸው በቂ ጥናት መደረጉን የሚያሳዩ ነገሮች አይታዩም።

አብዛኛዎቹ የመስተዳድሩ እንቅስቃሴዎች ገጽታ እና ምርጫ ተኮር ስለሆኑ የከተማዋን ገበና በእነዚህ ትላልቅ እና ከፍተኛ ገንዘብ በሚወስዱ ፕሮጀክቶች ለመሸፈን ጥድፊያም ላይ ያሉ ይመስላል። በሌላው ጎን ከንቲባው በአደባባይ የታሙባቸው እና ጠያቂ ቢኖር በሕግ በሚያስጠይቁ ተግባራት በማህበረ ድህረ ገጾችና በሚዲያ ሲብጠለጠሉ ቆይተዋል። ከዚህ በሚከተሉት ጉዳዬች መስተዳድሩ አንድም ጊዜ አጥጋቢ ምላሽ ሲሰጥ አልተስተዋለም፤

በሕገ ወጥ መንገድ ዘር ተኮር የነዋሪነት መታወቂያ ማደል፣

በአንድ ሰው መኖሪያ ቤት ባለቤቱ ሳያውቅ ለበርካታ ሰዎች ዘር ተኮር የመታወቂያ እና የቁጠባ ብድር መስጠት፣

በከተማዋ ፕላን መሰረት በየአካባቢው ለልጆች መጫወቻ እና ለልማት የተተው ክፍት ስፍራዎችን በሕገ ወጥ መንገድ እና ዘር ተኮር በሆነ መንገድ በግለሰቦች እጅ እንዲገቡ ማድረግ፣

ህገ ወጥ መኖሪያዎች በሚል የሚደረጉ ዘር ተኮር የቤት ማፍረስ እርምጃዎች፣

የከተማዋ ነዋሪ ከእለት ጉርሱ ቆጥቦ የሰራቸውን የመኖሪያ ቤቶች አሁንም ዘር ተኮር በሆነ መንገድ ለሌሎች አሳልፎ መስጠት፣

በከተማዋ መስተዳድር ውስጥ ዘር ተኮር የሆነ የሠራተኞች ድልድልና ሽግሽግ ማድረግ እና በሌሎች ተመሳሳይ ጥፋቶች በአደባባይ መስተዳድሩ እየተወነጀለ ነው።

እነዚህ ክሶች እውነት ተደርገው ከሆነ ሁለት ዋና የጥፋት አይነቶችን የያዙ ናቸው። አንደኛው ደድርጊቶቹ ለማንም ጥቅም ተብሎ ይፈጸሙ የአገሪቱን እና የከተማዋን ሕግ የጣሱ ናቸው። ሁለተኛው ጥፋት እያንዳንዱ ድርጊት ዘር ተኮር መሆኑ ነው። ሌሎቸን የህብረተሰብ ክፍሎች ለመጉዳት ሆን ተብሎ የተፈጸሙ ነው ባይባልም እንኳ አንድን ዘር ባልተገባ መልኩ፣ ስልጣንን ከለላ በማድረግ እና ሕግን በተላለፈ መልኩ ለመጥቀም የተፈጸሙ ናቸው መባሉ ነው።

በእነዚህ ክሶች ላይ መስተዳድሩ በድፍኑ አልፈጸምኩም ከማለት ባለፈ ወቀሳዎቹን በዝርዝር እና።በማስረጃ ሲያስተባብል አይታይም። የእነዚህን ጉዳዬች ክብደት ከግምት በማስገባት የፌዴራል መንግስቱ በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ መግባት እና ገለልተኛ አጣሪ አካል መድቦ ለእነዚህ የሕዝብ ብሶቶች በአፋጣኝ ምላሽ ቢሰጥ ጥሩ ነው። ይህን ቸል ማለት ድርጊቶቹ የፌደራል መንግስቱን የተቸሩ ያስመስላቸዋል። እነዚህን የሕዝብ ጥያቄዎች ወደ ጎን ለመግፋትም ሆነ በዳቦና በዘይት እደላ ለመሸፈን ከተሞከረ ግን ሌላ የፖለቲካ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም። አዲስ አበቤዎችም ያቄሙበትን ፖርቲ እንዴት መቅጣት እንደሚችሉ የሚያውቁበት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ምርጫ 97ን ማስታወሱ በቂ ነው።

LEAVE A REPLY