ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በትላንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሌት እና ውኃ አለቃቀቅ ደንብ ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ ምክክር ተደርጓል ብሏል።
ይህ ስብሰባ የተጠራው በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ፕሬዚዳንት በሆኑት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ እንደሆነና፤ ከሦስቱ አገራት በተጨማሪ የኬንያ፣ የማሊ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪዎች ተሳታፊ እንደነበሩ መግለጫው ያሳያል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ ከአፍሪካ የሚመነጭ መፍትኄ እንደሚያስፈልግ መሪዎቹ የተስማሙ ሲሆን፤ በውይይቱ ላይ ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መግለጫዎች መቅረባቸውንና ቀጣይ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውም ተገልጿል።
በግድቡ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንዲጠናቀቅ ስምምነት መደረጉን የሚያመለክተው መግለጫ፤
ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የግድቡን ቀሪ የግንባታ ሥራዎች በማጠናቀቅ ሙሌት ትጀምራለች፤ በእነዚህ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ደግሞ ሀገራቱ ከስምምነት ለመድረስ ተስማምተዋል ሲል ገልጿል።
በመጨረሻም የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን መመልከት መጀመሩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲገለጽ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ አባላት ድርድሩን እንዲደግፉ፣ ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ከቃላት መካረር እና አላስፈላጊ መግለጫዎች እንዲቆጠቡ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ሰሞኑን በተለይም ትናንትና እና ዛሬ የህዳሴ ግድቡን የውኃ ሙሌት በተመለከተ በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ከእውነት የራቀ ሀሰተኛ ዜና እያሰራጩ መሆናቸውም መንግሥት አስታውቋል።